በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው ኤርባስ ኤ350-1000 አውሮፕላን አዲስ አበባ ገባ - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው ኤርባስ ኤ350-1000 አውሮፕላን አዲስ አበባ ገባ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 26/2017(ኢዜአ)፦ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኤርባስ ኤ350-1000 አውሮፕላን አዲስ አበባ ገብቷል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኤር ባስ ኩባንያ የተረከበው የኤ 350-1000 አውሮፕላን ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሷል።
በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እየተካሄደ በሚገኘው አቀባበል የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ(ዶ/ር)፣ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን ኤ350-1000 "Ethiopia land of origins" የሚል ስያሜ የተሰጠውን የመንገደኞች አውሮፕላንን በትናንትናው ዕለት ከኤር ባስ የአውሮፕላን ኩባንያ መረከቡ ይታወቃል።
በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የኤ 350-1000 አውሮፕላን ለአየር መንገዱ ቀጣይ ዕድገት ትልቅ ስኬት ስለመሆኑ ተጠቅሷል።
የኤ350-1000 አውሮፕላን 400 መቀመጫዎች አሉት።
አየር መንገዱ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2035 በዓመት 67 ሚሊዮን መንገደኞችን በማጓጓዝ 25 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢ ለማግኘት እየሰራ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ባሉት 147 አውሮፕላኖች 139 ዓለም አቀፍ እና 22 የሀገር ውስጥ የበረራ መዳረሻዎችን እየሸፈነ ይገኛል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ አየር መንገዱ 124 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ማዘዙን መናገራቸው ይታወቃል።