ቀጥታ፡

ኮሌጁ ለአምራች ኢንዱስትሪዎችና ፋብሪካዎች የመለዋወጫ እቃዎችን በጥራት እያመረተ መሆኑን ገለጸ

ድሬደዋ፤ ጥቅምት 26/2017(ኢዜአ)፦ የድሬደዋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ለአምራች ኢንዱስትሪዎችና ፋብሪካዎች የመለዋወጫ እቃዎችን በጥራት እያመረተ መሆኑን ገለጸ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል የኮሌጁን የመለዋወጫ ዕቃዎች ምርቶች ከተመለከቱ በኃላ ስራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረው ነበር።

የኮሌጁ ዲን አቶ ሰለሃዲን አብዱልሃሚድ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ለኢንዱስትሪዎች የመለዋወጫ ዕቃዎችን በማምረት ምርታማነት እንዲጠናከር እያገዘ ነው።

ኮሌጁ ከኢንዱስትሪዎች ጋር ያለውን ትስስር በማጠናከር ሙያና ክህሎት የታጠቁ ባለሙያዎችን ከማቅረብ ባሻገር መለዋወጫዎችን በማምረት የውጪ ምንዛሬን እያዳነ ይገኛል ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ በምርት ሂደት የፋብሪካዎችን ችግሮች በጥናት በመለየት መፍትሄ እየሰጠ መሆኑንም ገልፀዋል።

እንደ ኮሌጁ ዲን አቶ ሰላሃዲን ገለፃ የተፈጠረው ትስስር የመምህራኑን የፈጠራ ብቃትና አዳዲስ ቴክኖሎጂ የማፍለቅ ጥበብ እንዲጨምር አስችሏል።

በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የኢትዮጵያ ታምርት ንቅንቄ ስኬታማ ለማድረግ ኮሌጁ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን አመልክተዋል።

በኮሌጁ የኢንዱስትሪ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ መሐመድ አወል በበኩላቸው ትስስሩ የኢንዱስትሪዎችን መሠረታዊ ችግሮች በቅርበት ለማወቅ ያስቻለና ለመፍትሄው በትኩረት ለመስራት ያነሳሳ መሆኑን ገልጸዋል።

በከተማዋ ለሚገኙት አምራች ኢንዱስትሪዎችና በነፃ ንግድ ቀጠና ውስጥ ለሚገኙ ፋብሪካዎች የተለያዩ የመለዋወጫ እቃዎችን በጥራት ተመርተዋል ብለዋል።

የኮሌጁ መምህራን ከመለዋወጫዎች በዘለለ በውጭ አገር ባለሙያዎች ሲከናወኑ የነበሩ ማሽኖችን የመግጠም እና ሼዶችን የመገንባት ተግባራትን ወደ ማከናወን መሸጋገራቸውንም አቶ መሐመድ ተናግረዋል።

ኮሌጁ የተለያዩ ማሽኖችን በመግጠም እና መለዋወጫዎችን በጥራት አምርቶ ተጠቃሚ ካደረጋቸው ፋብሪካዎች መካከል በድሬደዋ ነፃ ንግድ ቀጠና ውስጥ የተለያዩ የሲሚንቶ ከረጢቶችን የሚያመርተው ሃምፕላስ ፋብሪካ ተጠቃሽ ነው።

በፋብሪካው የምርት ክፍል ከፍተኛ ባለሙያ ወጣት መዘምር ወረደ እንደተናገረው፤ ኮሌጁ ለፋብሪካው ምርታማነት መጨመር መሠረታዊ ሚናን አበርክቷል።

የድሬዳዋ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የጀመራቸውን ስራዎች ሌሎቹም የአገራችን ኮሌጆች እንዲከተሉ ልምዱን እያካፈለ መሆኑን አመልክቷል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም