ከደመና በላይ የሚቀዝፈው የኢትዮጵያ ትዕምርት

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተቋም ብቻ አይደለም የአገር ምልክት ጭምር እንጂ። ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካውያን ኩራት የሆነ አድማስ ተሻጋሪ ስመጥር ተቋም ነው።

በውድድር የከበዳቸውን በሴራ ለማሳካት ብዙዎች የማሱለትን ጉድጓዶቹን እየደፈነ ፈተናዎችን በጥበብ እየተሻገረ የትውልድ ቅብብሎሽ ገናናነቱን አስጠብቆ 78 ዓመታትን ዘልቋል።

በዚህም ብዙ ክብር ብዙ ሞገስ አግኝቷል። ተቆጥረው የማያልቁ የምርጥ አየር መንገድነት ክብሮችን ተቀዳጅቷል። አስተማማኝነቱ እና የላቀ የደንበኞች አገልግሎቱ በአፍሪካ ግንባር ቀደም፣ በዓለም ደግሞ ተጠቃሽ ሆኖ እንዲቀጥል አስችለውታል።

በ1938 ዓ.ም የተቋቋመው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዚያው ዓመት የመጀመሪያ በረራውን ወደ ካይሮ ያደረገ ሲሆን ትንሿ ዳግላስ (Douglas C-47 Skytrain) የመጀመሪያዋ የአየር መንገዱ አድማስ ዘለል አውሮፕላን ነች።

በዚያው ዓመት አቅሙን በፍጥነት አሳድጎ መዳረሻውን በአፍሪካና ከአፍሪካ ውጭም ማስፋት ችሏል፡፡ የዕድገት ፍጥነቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደ ቦይንግ 720፣ 727፣ 737፣ 757፣ 767፣ 777 ያሉ ትላልቅና የላቀ ምቾት ያላቸው አውሮፕላኖች ባለቤት መሆን ቻለ። 

አየር መንገዱ የግዙፉ የአየር መንገዶች ጥምረት ስታር አሊያንስ አባል በሆነ በጥቂት ዓመታት ውስጥ በነዳጅ ቆጣቢነቱ የሚታወቀውን Airbus A350 XWB አውሮፕላን በመግዛት የመጀመሪያው የአፍሪካ አየር መንገድ ሆኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ አየር መንገዱ 124 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ማዘዙን መናገራቸው ይታወቃል፡፡

ይህ ብቻ ሳይሆን አየር መንገዱ በዓመት እስከ 130 ሚሊየን መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችል ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩም እንዲሁ፡፡

ይህም የኢትዮጵያ አየር መንገድን በአፍሪካ ትልቁ የአውሮፕላን ባለቤት ብቻ ሳይሆን ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ያለው ተቋም ያደርገዋል፡፡ 

አየር መንገዱ እያስመዘገበ ያለው ስኬት የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ማሳያ ሲሆን፤ በጀት ዓመቱ በአገልግሎት ዘርፍ 7 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ለማስመዝገብ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ሚናው የጎላ ነው፡፡

በአፍሪካ በቀዳሚነቱ እየገሰገሰ ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በየጊዜው ለአፍሪካ ማስተዋወቁን ቀጥሎበት በትላንትናው ዕለት የኤ350-1000 አውሮፕላን ከኤር ባስ ኩባንያ ተረክቧል።

Airbus A350-1000 የላቀ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ቴክኖሎጂ የተገጠመለት አውሮፕላኑ በአየር መንገዱ ምድረ ቀደምት (Ethiopia land of origins) የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡

ይህም አየር መንገዱ ለመንገደኞች ምቹ አገልግሎት የመስጠት አቅሙ እንዲጨምር ያደርጋል። 

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፤ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ኢትዮጵያ አጠቃላይ ሀገራዊ ሪፎርም ላይ ትገኛለች።

በአፍሪካ የመሪነት ሚናውን እየተወጣ ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአህጉሪቷ ኢኮኖሚ ትስስርን በመፍጠር የማይተካ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው ፣የኤ350-1000 አውሮፕላን ወደ ገበያው መግባት አየር መንገዱ የተያያዘውን ፈጣን እድገት በላቀ ደረጃ ለማሳለጥ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ አዳዲስ አውሮፕላኖችን በማስገባት ፈር ቀዳጅ መሆኑን በማንሳት፣ ኤ 350-1000 አውሮፕላንም በአየር መንገዱ ታሪክ ትልቅ ስኬት መሆኑን አክለዋል።

የኤር ባስ ኩባንያ ዓለም አቀፍ ዋና ስራ አስፈጻሚ ውተር ቫን ዌርሰች በበኩላቸው ይህ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የኤ350_1000 አውሮፕላን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ራዕይ 2035 ስኬት ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይ ጊዜያትም ኩባንያው ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በትብብር ለመስራት ትልቅ ፍላጎት አለው ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅትም ባሉት 147 አውሮፕላኖች 139 ዓለም አቀፍና 22 የሀገር ውስጥ የበረራ መዳረሻዎችን እየሸፈነ ይገኛል።

አየር መንገዱ በዓመት እስከ 130 ሚሊየን መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችል ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩም እንዲሁ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብሄራዊ ኩራትነቱ፣ የአገር ትዕምርትነቱ፣ የፓን አፍሪካ ምሳሌነቱ እና ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነቱ በጉልህ እየተንጸባረቀ ከደመና በላይ መቅዘፉን ይቀጥላል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም