ሀገራዊ ሪፎርም ከተጀመረ በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ የመጠባበቂያ ክምችት በእጥፍ አድጓል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ሪፎርም ከተጀመረ በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ የመጠባበቂያ ክምችት በእጥፍ አድጓል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 26/2017(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ሪፎርም ከተጀመረ በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ የመጠባበቂያ ክምችት በእጥፍ ማደጉን የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምሕረቱ አስታወቁ፡፡
አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ማሻሻያ አዋጅ ከዚህ ቀደም ለረዥም ዓመታት ሲሠራበት የቆየውንና ለዋጋ ንረት ዋና መነሻ ነበር ሲባል በቆየው አሠራር ላይ ጠበቅ ያለ የማሻሻያ ድንጋጌ ይዞ መቅረቡን የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምሕረቱ ከሴንትራል ባንኪንግ መጽሔት ጋር ባደረጉት ቆይታ አስታውቀዋል፡፡
የብሔራዊ ባንክ ግብ የፋይናንስና የዋጋ ንረትን ማረጋጋት እንደሆነ በመጥቀስ አዲሱ ረቂቅ አዋጅና፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጡ አዋጆችም ይህንኑ ግብ ለማሳካት በሚያስችል መንገድ ማሻሻያ እንደሚደረግባቸው ጠቅሰዋል፡፡
ይህን ተከትሎ ሀገራዊ ሪፎርሙ ከተጀመረ በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ የመጠባበቂያ ክምችት በእጥፍ ማደጉን ከመጽሔቱ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡
ለክምችቱ ማደግ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋምና የዓለም ባንክ ያደረጉት ድጋፍ፣ አበዳሪዎች እንደሚሰጡት የሚጠበቀው የብድር ክፍያ መራዘምና የወርቅ የወጪ ንግድ ግብይት በማዕከላዊ ባንክ በኩል እንዲያልፍ የተደረገው አሠራር ምክንያት መሆኑን በአብነት አንስተዋል፡፡
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ለኢትዮጵያ የሚያደርገው የፋይናንስ ድጋፍ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያን ለማሳለጥ ከፍተኛ እገዛ አለው ብለዋል፡፡
በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የሚተገበሩ የማሻሻያ ፕሮግራሞችን ኢትዮጵያ ቀደም ብላ መጀመሯን በማስታወስ፤ ለአብነትም የሞኒተሪ ፖሊሲ ማሻሻያና የዋጋ ንረትን ለመቀነስ የተወሰዱ እርምጃዎችን ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ የጀመረችው ጥረት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ኢኒሼቲቭ ከመጀመሩ ከዓመት በፊት መሆኑን በመጠቆም፤ በዚህም አመርቂ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የወለድ ምጣኔን መሠረት ያደረገ የሞኒተሪ ፖሊሲ እ.አ.አ. በነሐሴ 2023 መጀመሯን በመጥቀስ፤ በዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ብድር የመስጠት አቅም ማሳደግ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
በሀገሪቱ ያለው የዋጋ ግሽበት እ.አ.አ. በነሐሴ 2024 ላይ 17 በመቶ እንደነበርና ምግብ ነክ ያልሆኑ የፍጆታ ዕቃዎች የዋጋ ግሽበት 14 በመቶ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡
መንግሥት እየወሰዳቸው ባሉ የተለያዩ እርምጃዎች በቀጣይ ወራት የዋጋ ግሽበቱ እንደሚቀንስ ያላቸውን እምነትም ገልፀዋል፡፡
መንግሥት ክፍት ያደረገው የንግድ እንቅስቃሴ የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ ካለው አስተዋጽዖ በተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ማሻሻያውን ለማሳለጥ ሚናው የላቀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የውጭ ምንዛሬ ግብይትን በተመለከተ ከናይጄሪያ፣ ግብፅና ፓኪስታን ልምድ በመውሰድ ተግባራዊ እንደተደረገና የኢትዮጵያ አካሄድ በቀጣይ ገበያው የውጭ ምንዛሬ ሂደቱን እንዲመራው ማድረግ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ የጀመረችው ማሻሻያ በቀጣይ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አርዓያ እንደሚሆን ያላቸውን እምነትም ገልፀዋል፡፡
በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራት ለውጭ ገበያ የቀረበው የቡና፣ ወርቅና የቅባት እህል ግብይት በእጥፍ ማደጉን በመጠቆም፤ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ ምርቶች በአንፃሩ መቀነስ ማሳየታቸውን ገልፀዋል፡፡
እንዲሁም የባንኮች ተቀማጭ ገንዘብና ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ በሐዋላ የሚላከው ገንዘብ በእጅጉ እድገት ማሳየቱን ጠቅሰዋል፡፡
መንግሥት አሁንም የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል በነዳጅ፣ በማዳበሪያ፣ በመድኃኒትና በምግብ ዘይት ላይ ድጎማ ማድረግ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ሥልጣን የሚወስነው ሕግ ከሁለት ወራት በኋላ ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ በመጠቆም፤ ይህም የባንኩን ተወዳዳሪነት በእጅጉ እንደሚያሳድገው አስታውቀዋል፡፡
ሕጉ ባንኩ የዋጋ ምጣኔን ለማረጋጋት፣ የፋይናንስ ተቋማትን ህልውና ለማስጠበቅና ለኢኮኖሚ ዕድገቱ የራሱን አስተዋጽዖ እንዲያበረክት ሰፊ ዕድል እንደሚፈጥርለት ነው ያስረዱት፡፡
በኢትዮጵያ ያለው የባንክ ዘርፍ ላለፉት 40 ዓመታት ለውጭ ባንኮች ዝግ ሆኖ መቆየቱን በማስታወስ፤ የውጭ ባንኮች ተሳትፎ ተወዳዳሪነትን ለማስፋት፣ ቴክኖሎጂን ለማስረፅና የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን አጋዥ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ብሔራዊ የፋይናንስ ክፍያና ተደራሽነት ስትራቴጂ መቅረጿን ተከትሎ የተጀመረው ዲጂታል ፋይናንሲንግ ለመጀመሪያ ጊዜ በእጅ የሚፈጸመውን የገንዘብ ዝውውር መብለጡን ለስኬቱ ማሳያ በማድረግ አቅርበዋል፡፡
በቀጣይም በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ የብድር አገልግሎት፣ ዲጂታል ኢንቨስትመንትና ኢንሹራንስን ተደራሽ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል፡፡