ቀጥታ፡

ረሃብን በዘላቂነት ለማጥፋት ከምርታማነት ጋር የተያያዙ መዋቅራዊ ችግሮችን መፍታት ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 26/2017(ኢዜአ)፦ ረሃብን በዘላቂነት ለማጥፋት ከምርታማነት ጋር የተያያዙ መዋቅራዊ ችግሮችን መፍታት ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት በግብርና ምርታማነት ላይ ስትራቴጂካዊ ለውጥ በማምጣት ሰፋፊ ድሎችን ማስመዝገቧንም ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(ዩኒዶ)፣ የአፍሪካ ህብረት፣ የኢትዮጵያ መንግስት እና የዓለም የምግብ ድርጅት(ፋኦ) በጋራ ያዘጋጁት ከረሀብ ነፃ ዓለም /world without hunger/ ጉባኤ በአደዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው።

በጉባዔው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ የአቡዳቢ አልጋወራሽ ሼህ ኻሊድ ቢን መሃመድ ቢን ዛይድ፣ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት፣ የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዳይሬክተር ገርድ ሙለር እና ጥሪ የተደረገላቸው ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ፣ ከረሃብ ነጻ የሆነ ዓለም በመፍጠር ሂደት ውስጥ የአየር ጠባይ ለውጥና መዋቅራዊ ችግሮች ከፍተኛ ጫና እየፈጠሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ደግሞ ፈጠራ የታከለበት ችግር ፈቺ መፍትሄ ይሻል ነው ያሉት።


 

በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ ከመጣው የህዝብ ቁጥር አንጻር የምግብ ፍላጎት በእጅጉን ማደጉንም ነው ያነሱት።

ይህን ፍላጎት ለመመለስም ምርታማነትን ከማሻሻል በላይ በግብርና ዘርፍ ላይ የሚታዩ መዋቅራዊ ችግሮች መፍታት ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ብለዋል።

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት በግብርና ምርታማነት ላይ ስትራቴጂካዊ ለውጥ በማምጣት ሰፋፊ ድሎችን ማስመዝገቧን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የሚታረስ መሬትን በእጥፍ በመጨመር ምርታማነትን ማሻሻል ተችሏል ነው ያሉት።

በተለይ በስንዴ፣ በጤፍ፣ በቆሎ እና ገብስ ምርቶች ላይ ተጨባጭ ለውጥ ተመዝግቧል ብለዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመታ ብቻ 230 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ መመረቱን በማንሳት።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አማካኝነትም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ውጤታማ ስራ መከናወኑን ጠቅሰው፣ በመርሃ ግብሩም 40 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም