በአዳማ ከተማ የተጀመሩ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ስራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸው ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በአዳማ ከተማ የተጀመሩ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ስራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸው ተገለጸ
አዳማ፤ ጥቅምት 26/2017(ኢዜአ)፡- በአዳማ በከተማ ግብርና የተጀመሩ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ስራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን የከተማ ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አለሙ ቂልጡ ለኢዜአ አንደገለጹት፤ በከተማዋ የሰብል ልማት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የዶሮና የወተት ላሞች እርባታን ጨምሮ የንብ ማነብና የዓሣ ልማት ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ ነው።
በተለይም በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት አቮካዶ፣ ፓፓያ፣ ዘይቱን፣ ብርቱካን፣ ሙዝና ማንጎ በከተማ ግብርና እየለሙ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም 76 ሄክታር አቮካዶ፣ 68 ሄክታር ሙዝ፣ 46 ሄክታር ፓፓዬ፣ 32 ሄክታር ብርቱካንና ዘይቱን እየለማ ይገኛል ብለዋል።
በአጠቃላይ በስራው ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ ለ2 ሺህ 500 ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለም አስረድተዋል።
በከተማው እየተከናወነ ያለው የግብርና ልማት ስራ ገበያን ለማረጋጋትም እያገዘ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የከተማዋ የህብረት ስራ ማስፋፊያ ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዓለሙ ናቸው።
የግብርና ምርቶች በተለይ ቀጥታ ከአርሶ አደሩና አምራች ህብረት ስራ ማህበራት የእህልና የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በስድስት ማዕከላት ለገቢያ እየቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የግብርና ምርትን በማዕከላቱ በቀጥታ በአርሶ አደሩና በአምራች ማህበራት እንዲቀርብ በማድረግ በዋጋ ማረጋጋት ረገድ የጎላ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ነው ብለዋል።