በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ90 ሺህ በላይ ደንበኞች አዲስ ኃይል ተጠቃሚ ሆነዋል - የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ90 ሺህ በላይ ደንበኞች አዲስ ኃይል ተጠቃሚ ሆነዋል - የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 26/2017(ኢዜአ)፦ በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ሦስት ወራት ከ90 ሺህ በላይ ደንበኞች አዲስ ኃይል ተጠቃሚ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
አገልግሎቱ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸሙን አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።
የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ መላኩ ታዬ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ሦስት ወራት በርካታ አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
በሩብ ዓመቱ 120 ሺህ ደንበኞች የአዲስ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ 90 ሺህ 573 ደንበኞችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
አዳዲስ ደንበኞችን ጨምሮ የአገልግሎቱ ደንበኞች ከ4 ነጥብ 85 ሚሊየን በላይ መደረሱን ገልፀዋል።
በተጨማሪም አገልግሎቱ በመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከተለያዩ ገቢዎች ከ11 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ተናግረዋል።
ይህም ከዕቅዱ 97 በመቶ ሲሆን ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ41 በመቶ በላይ ብልጫ እንዳለውም ጠቁመዋል።
ገቢውም ከኃይል ሽያጭ፣ ከደንበኞች አገልግሎት፣ ካገለገሉ ዕቃዎች ሽያጭ እና ከሌሎች መሆኑን ገልፀዋል።