አቶ አረጋ ከበደ በወርኢሉ ወረዳ በኩታ ገጠም የለማ የስንዴ ሰብል ልማትን እየጎበኙ ነው

ደሴ ፤ ጥቅምት 26/2017(ኢዜአ)፡- የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እና ሌሎች አመራር አባላት በደቡብ ወሎ ዞን ወርኢሉ ወረዳ በኩታ ገጠም የለማ የስንዴ ሰብል ልማት እንቅስቃሴን እየጎበኙ ነው።

በዚህ ወቅት የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮንን እንደገለጹት፤ በዞኑ የስንዴ ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ ምርት በስፋት ለገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ነው።

በዚህም በመኸር ወቅቱ 200 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ መልማቱን ጠቁመው፤ ከዚህም ከ8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ለስንዴ ልማቱ በተሰጠው ልዩ ትኩረትም በቂ ግብዓት ከመጠቀም ባለፈ የዝናብ ስርጭቱ ምቹ መሆኑ፣ በአመራሩና ባለሙያ ድጋፍ መልማቱ ሰብሉ በተሻለ ቁመና ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ይህም የመኽር ወቅት ስንዴን ጨምሮ በሌሎች ሰብሎች 432 ሺህ ሄክታር መሬት መልማቱን ጠቅሰው፤ ከዚህም 14 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።

አሁን ያለው የሰብል ቁመና በሰብል ትንበያ ግምት ከእቅድ በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት በወርኢሎ ወረዳ በኩታ ገጠም ከለማ ስንዴ ሌላ በቀጣይም በጃማ ወረዳ የለማ ስንዴ ይጎበኛል ተብሎ ይጠበቃል።

በጉብኝቱ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር)፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎችም የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራር አባላት እየተሳተፉ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም