የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 26/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሰባተኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ፋሲል ከነማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።
በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው ፋሲል ከነማ በሊጉ ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ አንድ ጊዜ ተሸንፎ በአራቱ ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።
በጨዋታዎቹ አምስት ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ አምስት ግቦችን አስተናግዶ በሰባት ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በውድድር ዓመቱ እስከ አሁን ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ድል ሲቀናው አንድ ጊዜ ተሸንፎ በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል።
ቡድኑ ባደረጋቸው ጨዋታዎች አምስት ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ አራት ግቦች ተቆጥረውበት በዘጠኝ ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በሌላኛው የሰባተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ቡና ከስሑል ሽሬ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ ባከናወናቸው አምስት ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ሽንፈት አጋጥሞት አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
ቡናማዎቹ በጨዋታዎቹ ስድስት ግቦችን ሲያስቆጥሩ አምስት ጎሎች ተቆጥሮባቸው በሰባት ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ተጋጣሚው ስሑል ሽሬ በሊጉ ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን አንድ ጊዜ ሲሸነፍ በሶስቱ ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል።
በጨዋታዎቹ አምስት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ በተመሳሳይ አምስት ጎሎችን አስተናግዶ በስድስት ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ላይ ይገኛል።
በተያያዘም ትናንት በተደረጉ የሰባተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ኢትዮጵያ መድን መቀሌ 70 እንደርታን 4 ለ 0 ሲረታ መቻል አዳማ ከተማን 2 ለ 0 አሸንፏል።