የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የኤ350-1000 አውሮፕላን ዛሬ ከኤር ባስ ኩባንያ ተረከበ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የኤ350-1000 አውሮፕላን ዛሬ ከኤር ባስ ኩባንያ ተረከበ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን ኤ350-1000 "Ethiopia land of origins" የሚል ስያሜ የተሰጠውን የመንገደኞች አውሮፕላን ዛሬ ከኤር ባስ የአውሮፕላን ኩባንያ ተረክቧል ።
በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ ኢትዮጵያ አጠቃላይ ሀገራዊ ሪፎርም ላይ መሆኗን አንስተዋል ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ አየር መንገዱ 124 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ማዘዙን መናገራቸው ይታወቃል።
ይህ ብቻ ሳይሆን አየር መንገዱ በዓመት እስከ 130 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችል ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩም እንዲሁ፡፡
ይህም የኢትዮጵያ አየር መንገድን በአፍሪካ ትልቁ የአውሮፕላን ባለቤት ብቻ ሳይሆን ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ያለው ተቋምም ያደርገዋል።
አየር መንገዱ በዛሬው እለትም የኤ350-1000 የመንገደኞች አውሮፕላንን ተረክቧል።
በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ፣የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፣የአየር መንገዱ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ፣በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲ ለሚክ የኤር ባስ ኩባንያ ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ ፣ ኢትዮጵያ አጠቃላይ ሀገራዊ ሪፎርም ላይ መሆኗን አንስተዋል ።
በአፍሪካ የመሪነት ሚናውን ድርሻ እየተወጣ ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአህጉሪቷ ኢኮኖሚ ትስስርን በመፍጠር የማይተካ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።
አየር መንገዱ ዛሬ ከኤር ባስ ኩባንያ የተረከበውና በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የኤ 350_1000 አውሮፕላንም ለአየር መንገዱ ቀጣይ እድገት ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው ፣የኤ350-1000 አውሮፕላን ወደ ገበያው መግባት አየር መንገዱ የተያያዘውን ፈጣን እድገት በላቀ ደረጃ ለማሳለጥ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ አዳዲስ አውሮፕላኖችን በማስገባት ፈር ቀዳጅ መሆኑን በማንሳት፣ ኤ 350-1000 አውሮፕላንም በአየር መንገዱ ታሪክ ትልቅ ስኬት መሆኑን አክለዋል።
የኤር ባስ ኩባንያ ዓለም አቀፍ ዋና ስራ አስፈጻሚ ውተር ቫን ዌርሰች በበኩላቸው ይህ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የኤ350_1000 አውሮፕላን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ራዕይ 2035 ስኬት ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸዋል ።
በቀጣይ ጊዜያትም ኩባንያው ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በትብብር ለመስራት ትልቅ ፍላጎት አለው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኤ350-900 አውሮፕላኖችን ተረክቦ መስራት ከጀመረ ሰባት አመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም 20 ኤ350-900 አውሮፕላኖች በስራ ላይ ይገኛሉ።
በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የኤ350-1000 የመንገደኞች አውሮፕላን ከፈረንሣይ ቱሉስ ተነስቶ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ጥቅምት 26 ቀን 2017 ቀኑ 8 ፡00 ሰዓት ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከስፍራው ዘግቧል።