የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና የውሃ ሃብትን ለማጎልበት ትልቅ ሚና እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና የውሃ ሃብትን ለማጎልበት ትልቅ ሚና እያበረከተ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25/2017(ኢዜአ)፦የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ለውሃ ሀብት መጎልበት፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና የአፈር መሸርሸርን ለመጠበቅ ትልቅ ጠቀሜታ እያስገኘ መሆኑን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋ ገለጹ፡፡
"የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ለቀጣናው ዘላቂ የውሃ ሀብት አስተዳደር ያለው ሚና" በሚል መሪ ሃሳብ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት ዓለም አቀፍ የሃይድሮ ሜት ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) የኮንፈረንሱን የመጀመሪያ ቀን ውሎ አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፥ በኮንፈረንሱ የአረንጓዴ አሻራ በኢትዮጵያ የውሃ ሀብትና በቀጣናው ያመጣው ለውጥ መቅረቡን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ጉባዔው በዓለም ላይ እያጋጠመ ያለውን ድርቅ መቋቋም በሚያስችል ሁኔታ ላይ መረጃዎችን ለመለዋወጥ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ በመወያየት መግባባት ላይ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት 40 ቢሊዮን ችግኞችን መትከሏን የተናገሩት ሚኒስትሩ የተተከሉ ችግኞች የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥና ከስራ ዕድል ፈጠራ ባሻገር ለውሃ ሃብት መጎልበት አዎንታዊ ተጽእኖ ማሳደራቸውን ተናግረዋል፡፡
በአባይ ተፋሰስ፣ በስምጥ ሸለቆ እና በላይኛው የአዋሽ ተፋሰስ ላይ በተከናወኑ የምርምር ስራዎች ከዚህ ቀደም የተራቆቱ ቦታዎች በደን መሸፈን መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡
በአባይ ተፋሰስ ከአራት እስከ አምስት በመቶ የደን ሽፋን እንዲጨምር ማስቻሉን ጠቁመው በሁሉም ተፋሰሶች ላይ የሚታዩ ለውጦች መመዝገባቸውን ጠቁመዋል፡፡
በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ ችግኞች በውሃ ሃብት መጎልበት ትልቅ አስተዋጽኦ መጫወታቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ጎርፍ ሆኖ ጉዳት እንዳያደርስና ወደ ከርሰ ምድር እንዲገባ ማስቻልን ጨምሮ የአፈር እርጥበት እንዲጨምር ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
በሌላ መልኩም የመሬት መሸርሸርን በመከላከል የግድቦችን ደህንነት ከማስጠበቅ አንጻር ጉልህ ሚና መጫወቱን ጠቁመው የግድቦችን የደለል መጠን ከመቀነስ አንጻርም አዎንታዊ ምላሾች መታየት መጀመራቸውን ጠቁመዋል፡፡
ከአየር ትንበያ አኳያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም መረጃዎችን ቀድሞ በማጋራት የሚከሰተውን አደጋ መቀነስ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
እንደ ሀገር የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በተሰሩ ስራዎች በአባይ ተፋሰስ እና በሁሉም ቦታዎች ውጤት መታየት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተወጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች መታደማቸውን ያነሱት ሚኒስትሩ ለልምድ ልውውጥ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ነገም በሚቀጥለው የዓለም አቀፍ ሃይድሮ ሜት ኮንፈረንስ ከውሃ ሀብት ልማት ባሻገር የአየር ትንበያ ስርዓትና ጠንካራ የመረጃ አቅም እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ምክክር እንደሚደረግ ይጠበቃል።