ቀጥታ፡

የኃይማኖት ተቋማት ልዩነቶችን በማጥበብ አንድነትን ለማጠናከር የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25/2017(ኢዜአ)፦የኃይማኖት ተቋማት ልዩነቶችን በማጥበብ አንድነትን ለማጠናከር የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ሲሉ  የኢፌዴሪ  ፕሬዝዳንት  ታዬ አፅቀ ሥላሴ ተናገሩ።

የሰላም ሚኒስቴር በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ከሚገኘው ከመሐመድ ቢን ዛይድ ፎር ሂዩማኒቲ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ዓለም አቀፍ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ  በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው። 

በጉባዔው መክፈቻ የኢፌዴሪ  የፕሬዝዳንት  ታዬ አፅቀ ሥላሴ ጨምሮ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም፣ የመሐመድ ቢን ዛይድ ፎር ሂዩማኒቲ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ካልፍ ሙባረክ (ዶ/ር)፣ የኃይማኖቶች አባቶች፣ የኢትዮጵያ  የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ፣ በኃይማኖትና በሰላም ጥናትና ምርምር ያካሄዱ ዩኒቨርሲቲዎች ተሳትፈዋል።

እንዲሁም የምስራቅ አፍሪካ፣የሩስያ፣የሞሮኮና የደቡብ አፍሪካ የኃይማኖት ተቋማት፣ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በጉባዔው ላይ ተገኝተዋል።

የኢፌዴሪ  የፕሬዝዳንት  ታዬ አፅቀ ሥላሴ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጽንፈኝነትና የመከፋፈል ኃሳብ አብሮ ለመኖር አደጋ እየሆነ መጥቷል። 

በመሆኑም ኃይማኖት ተቋማት ለአብሮነትና መቻቻል አደጋ እየሆነ የመጣውን የጽንፈኝነትና የመከፋፈል ኃሳብ ለማስወገድ በቁርጠኝነት መሥራት እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት።

የኃይማኖት ተቋማት ልዩነቶችን በማጥበብ አንድነትን ለማጠናከር የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባም ተናግረዋል። 

ለዚህም የኃይማኖት ተቋማት የመቻቻል፣ አብሮ የመኖርና የመተሳሰብ እሴት በማጠናከረ ረገድ ሚናቸው የጎላ መሆኑንም በመጠቆም። 

በመሆኑም በጉባዔው የኃይማኖት ተቋማት አገራዊ አንድነትን በሚያጠናክሩበት፣ የጋራ ተግዳሮቶችን  በጋራ ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች በትኩረት መምከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። 

ኢትዮጵያን ብዝኃ-ኃይማኖቶች በጋራ ተቻችለው የሚኖሩባት በመሆኑ ለዓለም ትልቅ ምሳሌ መሆኗን ፕሬዝዳንቱ አንስተዋል።

የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም በበኩላቸው፤ የኃይማኖት ተቋማት ሰላምን በማስፈን ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።


 

አሁን ላይ በዓለም ላይ እያጋጠሙ ያሉ የመከፋፈል ችግሮችን ለመፍታት የኃይማኖት ተቋማት የመቻቻል ትርክትን መገንባት ላይ መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።  

የኃይማኖት መሪዎችና ተቋማት በተለያዩ እምነቶች መካከል ውይይትና መግባባትን መፍጠር፣ የተዛባ አመለካከትን ማፍረስ እንዲሁም መከባበርን ማጎልበት ላይ አበክረው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው፤ ሁሉም ኃይማኖቶች ሰላምን፣ አንድነትን፣ ፍቅርን፣ መረዳዳትን እንዲያስተምሩና እንዲሰብኩ ኃላፊነት ከፈጣሪ የተሰጣቸው መለኮታዊ ተቋማት መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

በዚህ ረገድ  ተቋማቱ የሰው ልጆች ያላቸውን ልዩነት በማቻቻል በአንድነትና በፍቅር እንዲኖሩ ማስተማር አለባቸው ብለዋል።

መለያየት ተገቢ አለመሆኑን የኃይማኖት አባቶች በቃልና በተግባር ለተከታዮቻቸው ማስገንዘብ እንዳለባቸውም ተናግረዋል። 

ልዩነቶች እንደተጠበቁና እንደተከበሩ ሆነው ዜጎች በመቻቻልና በመከባበር በሰላምና በአንድነት እንዲኖሩ መሥራት አለብን ብለዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም