የዓለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25/2017(ኢዜአ)፦የዓለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት (ኢልሪ) በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ለመጨመር የሚያከናውነውን ዘርፈ ብዙ ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ።
የዓለም አቀፍ እንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት ኢትዮጵያ ሥራ የጀመረበትን 50 ዓመት በዓል በተመለከተ የውይይት መርኃ ግብር አዘጋጅቷል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ባለፉት 50 ዓመታት የግብርና ሚኒስቴር ከዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በትብብር ሲሰራ ነበር።
ዓለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ የእንስሳት ዝርያዎችን ለማዳቀል በምርምር የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎች እንዲወጡ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ በእንስሳት ጤና አጠባበቅ፣ በመኖ ዝግጅትና የተሻሻለ የእንስሳት አያያዝ ሥርዓት እንዲኖር ከኢትዮጵያ የምርምር ማዕከላት ጋር የላቀ ሚና ተወጥቷል ብለዋል።
በኢትዮጵያ በእንስሳት እርባታ በሚተዳደሩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተሻለ የእንስሳት አያያዝ ሥርዓት እንዲፈጠር በትብብር መሥራቱን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለጀመረችው የሌማት ትሩፋት መርኃ ግብር የሥጋ፣ ወተትና ወተት ተዋፅዖ በስፋት ለማምረትና ለማቅረብ ወሳኝ አጋር መሆኑን ገልጸዋል።
የዓለም አቀፍ እንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፖሊኔይር ዲጂኪንግ፤ ዓለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት ባለፉት 50 ዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።
በእንስሳት ማዳቀል፣ ጤናና መኖ ዝግጅት እንዲሁም አቀራረብ ላይ የተሰሩ የምርምር ሥራዎች ከኢትዮጵያ የግብርና ስትራቴጂ ጋር የተጣጣሙ እንደነበሩ እንስተዋል።
ለአብነትም በኢትዮጵያ የወተት ምርትን ለማሳደግ ለአነስተኛ አምራቾች የገበያ ትስስር ለመፍጠር የተጀመረው የወተት ልማት ፕሮግራም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ከድኅነት አውጥቷል ብለዋል።
በኢትዮጵያ በእንስሳት እርባታና በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ በዝቅተኛ ኢኮኖሚ የሚተዳደሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ከድኅነት ለማውጣት እየተሰራ ያለው ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር አማካሪ ቡድን የኢትዮጵያ ተወካይ ናሙኮሎ ኮቪክ ዓለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት በግብርናው መስክ በምርምር የተደገፈ መረጃ በመስጠት የጎላ አበርክቶ ነበረው ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ትብብር የላቀ እንደነበር አንስተዋል።