የሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የግብርና ልማት የሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ገለጸ::
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከአጋር አካላት ጋር በመሆን " ሰው ሰራሽ አስተውሎት ለግብርና ምርምርና ምግብ ስርዓት ዕድገት " በሚል መሪ ሃሳብ ለሶስት ቀናት የሚቆይ የባለድርሻ አካላትና የተመራማሪዎች ስልጠና ጀምሯል፡፡
የኢትዮጵያ አርተፊሻል ኢንተሊጀንስ ኢንስቲትዩት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን በግብርና፣ ጤና ፣ ትምህርት እና መንግስት አስተዳደር ዘርፎች በመጠቀም እመርታ እያስመዘገበ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ በዚሁ ወቅት፤ የግብርናውን ዘርፍ የሚያሳድጉ የሰው ሰራሽ አስተውሎት መተግበሪያዎችን ጥቅም ላይ ማዋል አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
የሰው ሰራሽ አስተውሎት በግብርናው ዘርፍ ጥቅም ላይ መዋሉ በልማቱ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አርተፊሻል ኢንተለጀንስ የምርምር ስራዎች ፈጣን፣ ጥራታቸው የተጠበቀ ብሎም ውጤታማነታቸውን ይበልጥ ከማረጋገጥ አንጻር ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል፡፡
አርተፊሻል ኢንተለጀንስ የኢትዮጵያን ግብርና ለማዘመንና ውጤታማነቱን ለማሳደግ እንደሚረዳ ጠቁመው ለሀገሪቱ ግብርና ትልቅ አስተዋጽኦ ይጫወታል ብለዋል፡፡
የሰው ሰራሽ አስተውሎትን የመሬት ጥንካሬና ልስላሴን ለመለየት፣ ለአረም፣ ማዳበሪያን መጥኖ ለመጨመር እንዲሁም ለመስኖ ልማት ለመጠቀም እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
አርሶአደሮች ቴክኖሎጂውን አውቀው እንዲጠቀሙ በባለሙያ አማካኝነት የማውረድና ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ በቀጣይ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ የግብርናው ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ቴክኖሎጂዎቹ ጥቅም ላይ እንዲውሉ መስራት አለባቸው ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታዬ ግርማ (ዶ/ር) ኢንስቲትዩቱ በግብርናው ዘርፍ በቲማቲም በሽታ እና ቅጠል ላይ መሰረት ያደረገ እንዲሁም የቡና በሽታ ልየታ ስራ ማከናወኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም መተግበሪያዎችን በመፍጠር አርሶ አደሩ በቀላሉ እንዲጠቀም መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜም ከግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በዶሮ እና እንስሳት እርባታ ዙሪያ ምርምሮችን ለመስራት በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ባይሳ በዳዳ በበኩላቸው ሰው ሰራሽ አስተውሎት የኢትዮጵያ ግብርና ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን የሚያግዝ በመሆኑ ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል ብለዋል፡፡
እንደ ሀገር አርተፊሻል ኢንተሊጀንስን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ለአካባቢ ዘላቂ ልማት እንዲሁም ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና መጠቀም እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
ለሶስት ቀናት የሚቆየውን ስልጠና የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ አርተፊሻል ኢንተሊጀንስ ኢንስቲትዩት፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በጋራ አዘጋጅተውታል፡፡