ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለቀጣናው የውኃ ኃብት ዘላቂ ልማት የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ለቀጣናው የውኃ ኃብት ዘላቂ ልማት የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

አገራት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ሊከሰት የሚችል የውኃና አየር ሁኔታ መዛባትን ለመከላከል ጠንካራ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት መገንባት አለባቸው ብለዋል።

ዓለም አቀፍ የሃይድሮሜት ጉባኤ "የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ለቀጣናው ዘላቂ የውኃ ኃብት ልማት እመርታ" በሚል መሪ ኃሳብ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በኮንፈረንሱ ባደረጉት ንግግር፤ የዘመናችን ዋና ፈተና የሆነው የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም ላይ ድርቅን፣ የጎርፍ መጥለቅለቅንና አስቸጋሪ የአየር ሁኔታን ማስከተሉን ገልጸዋል። 

በዚህ የተነሳም ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ አገራት ኢኮኖሚ ከፍተኛ ጉዳት መፈጠሩን ጠቅሰዋል።

አፍሪካ በተለይም የምስራቅ አፍሪካ አገራት የተፅዕኖው ዋና ገፈት ቀማሽ  ናቸው ያሉት አቶ ተመስገን፤ ድርቅና ጎርፍ ለረጅም ጊዜ የማይጠፉበት ቀጣና መሆኑንም ተናግረዋል።


 

ኢትዮጵያ በ2011 ዓ.ም በጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ለችግሩ ፈር ቀዳጅ  መፍትሔ በመውሰድ ለዓለም ማሳየቷን ገልጸዋል።

በመርኃ ግብሩ  እስካሁን 40 ቢሊዮን ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፤ ይህም የደን ሽፋንን በማሳደግ፣ የአፈር መሸርሸርን በመከላከል፣ የውኃ ኃብቶቻችንን በማጎልበትና አካባቢን በመጠበቅ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ከራሷ ባለፈ ለቀጣናው ዘላቂ አካባቢና የውኃ አካላት ጥበቃ የሚተርፍ ሚናዋን በመወጣት ትክክለኛ መሪነቷን በማሳየት ላይ ናት ብለዋል።

ለአብነትም ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ ወንዞቿን ዘላቂነት በማረጋገጥም ለጎረቤት አገራት ትልቅ አበርክቶ መወጣቷን በመጥቀስ።

ባለፈ ስኬት መኩራራት ብቻ ሳይሆን አደጋዎችን ለማስቀረት የኃይድሮ ሚቲዎሮሎጂ እርምጃዎቻችንን ማዘመን፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶችን በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ ማድረግ፣ ድንበር ዘለል ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።


 

የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ፕሬዝዳንት አብዱላ አህመድ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ በረሃማነትን በመከላከልና የውኃ ኃብትን በማጎልበት ረገድ ለዓለም ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል።

በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የውኃ አካላት ከፍተኛ ጉዳት ማስተናገዳቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገራት በድርቅና በጎርፍ መጠቃታቸውን ጠቅሰው፤ ይህም አፋጣኝና የተቀናጀ  ጥረትን ይፈልጋል ነው ያሉት።

የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የውኃ ኃብት አስተዳደርና የሚቲዎሮሎጂ ትንበያ አቅምን ለማሻሻል በዓለም አቀፍ ደረጃ እየሠራ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።


 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም