የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የቡና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ግብዓቶችን ለአራት ክልሎች ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የቡና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ግብዓቶችን ለአራት ክልሎች ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን በ3 ሚሊየን ዶላር የተገዙ የቡና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ግብዓቶችን ለአራት ክልሎች ድጋፍ አደረገ።
ድጋፉ የተደረገው ለኦሮሚያ፣ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ለሲዳማና ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ነው።
ግብዓቶችን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት ለአራቱም ክልሎች ተወካዮች አስረክበዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ባለፉት ዓመታት የቡና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራት አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በ2016 በጀት ዓመት ብቻ 300 ሺህ ቶን ቡና ኤክስፖርት በማድረግ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 1 ነጥብ 43 ቢሊየን ዶላር ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል።
ባለሥልጣኑ በቀጣይ ከቡና የሚገኘውን ምርት ከዚህ በላይ ለማሳደግ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
ለዚህም ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት መርኃ-ግብር (ዩ ኤን ዲ ፒ) ለሰባት ዓመታት የሚውል የ9 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ማግኘቱን ገልፀዋል።
ከዚህ ውስጥ በ3 ሚሊየን ዶላር የተለያዩ የቡና ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ግብዓቶችን በመግዛት ለአራቱ ክልሎች እንዲሰራጩ መደረጉን ተናግረዋል።
ድጋፉ በሞተር የሚሰሩ መጋዞች፣ የጉድጓድ መቆፈሪያና ሌሎች መሣሪያዎች ተካተውበታል ብለዋል።
ግብዓቶቹ የቡና ምርትና ምርታማነታችንን በማሳደግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የቡና ምርት ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑን የክልሎቹ ተወካዮች አረጋግጠዋል።