ቴክኖሎጂን አልምቶ በመጠቀምና የፈጠራ ባለቤቶችን መብት በማስጠበቅ የኢኮኖሚ እድገቱን ለማፋጠን እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ቴክኖሎጂን አልምቶ በመጠቀምና የፈጠራ ባለቤቶችን መብት በማስጠበቅ የኢኮኖሚ እድገቱን ለማፋጠን እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂን አልምቶ በመጠቀምና የፈጠራ ባለቤቶችን መብት በማስጠበቅ የኢኮኖሚ እድገቱን ለማፋጠን የጀመረችው ተግባር ለሌሎች ተሞክሮ የሚሰጥ መሆኑን በዓለም አእምሯዊ ንብረት ድርጅት የአፍሪካ ዲቪዥን ተጠባባቂ ዳይሬክተር ሎሬታ አሲዱ ገለፁ።
የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን አገር አቀፍ የአዕምሮዊ ንብረት ሳምንትን አስመልክቶ ለሁለት ቀን የሚቆይ አውደ ጥናት ማካሄድ ጀምሯል።
በአውደ ጥናቱ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን፣ በዓለም አእምሯዊ ንብረት ድርጅት የአፍሪካ ዲቪዥንና የጃፓን የፓተንት ጽህፈት ቤት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
በዓለም አእምሯዊ ንብረት ድርጅት የአፍሪካ ዲቪዥን ተጠባባቂ ዳይሬክተር ሎሬታ አሲዱ እንዳሉት የፈጠራና የቴክኖሎጂ ውጤቶች የአለምን ኢኮኖሚ በፍጥነት በማሳደግና የስራ ዕድል በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ነው ።
ፈጠራና ቴክኖሎጂ ድህነትንና ኋላቀርነትን በማስቀረት የአለምን የኢኮኖሚ እድገት በፍጥነት እየለወጠ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ የፈጠራ ባለቤቶችን በማፍራትና በመጠበቅ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጡ ተግባራት እያከናወነች መሆኑን በበጎ አንስተዋል፡፡
የፈጠራና የቴክኖሎጂ ልማት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በዘላቂነት እንዲፋጠን እያደረገው መሆኑን መገንዘባቸውንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂን በማልማት ኢኮኖሚዋን በዘላቂነት ለማሳደግ የጀመረችው ተግባር ለሌሎች ልምድና ተሞክሮ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወልዱ ይመስል አውደ ጥናቱ የኢንተርፕራይዞችን የአዕምሮ ንብረት ግንዛቤና ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ለኢኮኖሚ እድገት ሚናቸውን እንዲወጡ ታስቦ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂን አልምቶ በመጠቀምና የፈጠራ ባለቤቶችን መብት በማስጠበቅ የኢኮኖሚ እድገቱን ለማፋጠን እየሰራች መሆኑን ገልፀዋል።
የፈጠራ ባለቤቶችን በፋይናንስ በመደገፍ ጥራት ያለውና ተወዳዳሪ ምርት ለገበያ እንዲያቀርቡ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።