የኃይማኖት ተቋማት ፅንፈኝነትና የመከፋፈል እሳቤን ለማስወገድ በቁርጠኝነት መስራት አለባቸው - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
የኃይማኖት ተቋማት ፅንፈኝነትና የመከፋፈል እሳቤን ለማስወገድ በቁርጠኝነት መስራት አለባቸው - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25/2017(ኢዜአ)፦ የኃይማኖት ተቋማት ለዓለም ፈተና እየሆነ ያለውን የፅንፈኝነትና የመከፋፈል እሳቤን ለማስወገድ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ተናገሩ።
የሰላም ሚኒስቴር በዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ ከሚገኘው ከመሐመድ ቢን ዛይድ ፎር ሁማኒቲ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ዓለም አቀፍ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው ።
በጉባኤው መክፈቻ የኢፌዴሪ የፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ጨምሮ የሠላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም ፣የመሐመድ ቢን ዛይድ ፎር ሁማኒቲ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ዶክተር ካልፍ ሙባረክ፣ የሃይማኖቶች አባቶች ፣የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ፣ በኃይማኖትና በሰላም ጥናትና ምርምር ያካሄዱ ዩኒቨርሲቲዎች ተሳትፈዋል።
እንዲሁም የምስራቅ አፍሪካ፣ የሩሲያ፣ የሞሮኮ እና የደቡብ አፍሪካ የሃይማኖት ተቋማትና አለም አቀፍ ድርጅቶች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በጉባዔው ላይ ተገኝተዋል።
የኢፌዴሪ የፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የኃይማኖት ተቋማት የመቻቻል፣ አብሮ የመኖርና የመተሳሰብ እሴት በማጠናከረ ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያንም ብዝሃ ኃይማኖቶች በጋራ ተቻችለው የሚኖሩባት በመሆኑ ለዓለም ትልቅ ምሳሌ እንደሆነች አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅት ዓለም ላይ የፅንፈኝነትና የመከፋፈል ሀሳብ አብሮ ለመኖር አደጋ እየሆነ መምጣቱ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
ኃይማኖት ተቋማት ለአብሮነትና መቻቻል አደጋ የሆነው የፅንፈኝነትና የመከፋፈል ሀሳብ ለማስወገድ በቁርጠኝነት መስራት አለባቸው ብለዋል።
በጉባኤው የኃይማኖት ተቋማት ሀገራዊ አንድነትን በሚያጠናክሩበት፣ የጋራ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በትኩረት መምከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የሠላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም በበኩላቸው የሃይማኖት ተቋማት ሰላምን በማስፈን ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል።
አሁን ላይ በዓለም ላይ እያጋጠሙ ያሉ የመከፋፈል ችግሮች ለመፍታት የኃይማኖት ተቋማት የመቻቻል ትርክትን መገንባት ላይ መስራት አለባቸው ብለዋል።
የኃይማኖት መሪዎች እና ተቋማት በተለያዩ እምነቶች መካከል ውይይት እና መግባባትን መፍጠር፣ የተዛባ አመለካከትን ማረም እና መከባበርን ማጎልበት ላይ አበክረው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
በኮንፈረንሱ ላይ ከ16 ሀገራት የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶችና የተቋማት መሪዎች እየተሳተፉ ነው።