ኢትዮጵያ ለዘላቂ የውሃ ሀብት አስተዳደር የሰጠችው ትኩረት ለጎረቤት ሀገራት ትልቅ ሚና አለው -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለዘላቂ የውሃ ሀብት አስተዳደር የሰጠችው ትኩረት ለጎረቤት ሀገራት ትልቅ ሚና አለው -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለዘላቂ የውሃ ሀብት አስተዳደር የሰጠችው ትኩረት ለጎረቤት ሀገራት ትልቅ ሚና አለው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ፡፡
ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ሊከሰት የሚችል የውሃና አየር ሁኔታ መዛባትን ለመከላከል ጠንካራ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት መገንባት አለባቸው ብለዋል።
"የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ለቀጣናው ዘላቂ የውሃ ሀብት አስተዳደር ያለው ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት ዓለም አቀፍ የሃድሮሜት ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በኮንፈረንሱ ባደረጉት ንግግር፥ የዘመናችን ዋና ፈተና የሆነው የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም ላይ ድርቅን፣ የጎርፍ መጥለቅለቅን እና አስቸጋሪ የአየር ሁኔታን ማስከተሉን ገልጸዋል።
በዚህ የተነሳም ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ሀገራት ኢኮኖሚ ከፍተኛ ጉዳት መፈጠሩን ጠቅሰዋል።
አፍሪካ በተለይም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተፅዕኖው ዋና ገፈት ቀማሽ ናቸው ያሉት አቶ ተመስገን፥ ድርቅና ጎርፍ ለረጅም ጊዜ የማይጠፉበት ቀጣና መሆኑንም ተናግረዋል።
በመሆኑሞ ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ የተግባር እርምጃ መውሰድ አለብን ብለዋል።
ኢትዮጵያ በ2011 ዓ.ም በጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ለችግሩ ፈር ቀዳጅ መፍትሔ በመውሰድ ለዓለም ማሳየቷን ገልጸዋል።
በመርሐ ግብሩ እስካሁን 40 ቢሊዮን ችግኞችን የተከለች ሲሆን፤ ይህም የደን ሽፋንን በማሳደግ፣ የአፈር መሸርሸርን በመከላከል፣ የውሃ ሀብቶቻችንን በማጎልበትና አካባቢን በመጠበቅ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ከራሷ ባለፈ ለቀጣናው ዘላቂ አካባቢና የውሃ አካላት ጥበቃ የሚተርፍ ሚናዋን በመወጣት ትክክለኛ መሪነቷን በማሳየት ላይ ናት ብለዋል።
ለአብነትም ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ ወንዞቿን ዘላቂነት በማረጋገጥም ለጎረቤት ሀገራት ትልቅ አበርክቶ መወጣቷን በመጥቀስ።
ሆኖም ባለፈ ስኬት መኩራራት ብቻ ሳይሆን አደጋዎችን ለማስቀረት የሃይድሮ ሚቲዎሮሎጂ እርምጃዎቻችንን ማዘመን፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓቶችን በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ ማድረግ፣ ድንበር ዘለል ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በአፍሪካ ላይ ከሚደርሰው የአየር ንብረት ለውጥ ጫና 50 በመቶው ምስራቅ አፍሪካ ላይ የሚያርፍ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለድርቅና ጎርፍ ዘላቂ መፍትሔን ለማምጣት በተገበረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የውሃ ምንጮች እየጎለበቱ ሲሆን ይህም ለቀጣናው ጭምር ፋይዳው የላቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የአየር ንብረት ለውጥ ጫናን በጋራ በመቀነስ ዘላቂ የውሃ ሀብት አስተዳደርን መገንባት ይገባል ነው ያሉት።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)፣ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የአፈር መሸርሸር፣ በረሃማነትና የብዝኃ ህይወት መመናመን ከፍተኛ ጉዳት ማስከተላቸውን አውስተዋል።
የአፈር መሸርሸር ለረዥም ዓመታት በኢትዮጵያ አርሶ ደሮች ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮ መቆየቱን ጠቅሰዋል።
የአፈር ለምነትን በመቀነስ ምርታማነት እንዳያድግ ከማድረጉ ባለፈ ግድቦች በደለል እንዲሞሉ በማድረግ ትልቅ ተግዳሮት ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል።
ችግሩን ለመፍታት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር የኢትዮጵያን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባትና ለዘላቂ የአካባቢ ጥበቃ ያላትን ጽኑ አቋም የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በዚህም የተራቆቱ አካባቢዎች እያገገሙ መምጣታቸውን ገልጸው፥ የአፈር መሸርሸር መጠን እና ወደ ውሃ አካላት የሚገባው ደለል በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን ገልጸዋል።
የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ፕሬዚዳንት አብዱላ አህመድ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ በረሃማነትን በመከላከልና የውሃ ሀብትን በማጎልበት ረገድ ለዓለም ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል።
በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የውሃ አካላት ከፍተኛ ጉዳት ማስተናገዳቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት በድርቅን በጎርፍ መጠቃታቸውን ጠቅሰው፤ አፋጣኝና የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የውሃ ሀብት አስተዳደርና የሚቲዎሮሎጂ ትንበያ አቅምን ለማሻሻል በዓለም አቀፍ ደረጃ እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት።