ቀጥታ፡

የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የወጪ ንግድ ግኝትን ለማሳደግ የተጀመሩ የአሰራር ማሻሻያዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጸ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25/2017(ኢዜአ)፦ የወጪ ንግድ ግኝትን ለማሳደግ የተጀመሩ የአሰራር ማሻሻያ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገልጿል።

የንግድ  እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የ2017 በጀት ዓመት የ1ኛ ሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማውን በማካሄድ ላይ ይገኛል። 

የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ወሀብረቢ በበጀት ዓመቱ የወጪ ንግድ ገቢን ለማሳደግ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት  ምቹ እና አማራጭ የግብይት ስርአት በመፍጠር የወጪ ንግድ ግኝትን ማሳደግ እንደሚገባ አመልክተዋል።


 

ምርትን በወቅቱ ለገበያ ማቅረብ ከኤክስፖርት የሚገኘውን ገቢ ለመጨመር እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

በቅባት እህሎች እና የጥራጥሬ ምርቶች ላይ ተግባራዊ የተደረገው ቀጥታ የግብይት ስርዓት የወጪ ንግዱን እንደሚያሳልጥም ተናግረዋል። 

የአሰራር ስርዓትን በማሻሻል ኮንትሮባንድን ማስወገድ እና የምርት ነጻ እንቅስቃሴን የሚገድቡ ኬላዎችን ማንሳት እንደሚገባ ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ የገለጹት።

መንግስት ያለ አግባብ በሚደረግ የምርት ክምችት፣ ኮንትሮባንድ እና ሕገ-ወጥነት ላይ የተቀናጀ ቁጥጥር እንደሚያደረግም አስገንዝበዋል።

የወጪ ንግድ ግኝትን ለማሳደግ የተጀመሩ የአሰራር ማሻሻያ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ መናገራቸውን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ የወጪ ንግድ ምርቶች የሚመረትባቸው አካባቢዎች የወጪ ንግድን የትኩረት አቅጣጫቸው አድርገው መስራትና አቅርቦቱን ማሳደግ እንዳለባቸው አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም