አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ ከጂቡቲ የቱሪዝም እና የሚዲያ ባለሙያዎች ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ ከጂቡቲ የቱሪዝም እና የሚዲያ ባለሙያዎች ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24/2017(ኢዜአ)፦በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገው ከተመለሱ የጂቡቲ የቱሪዝምና የሚዲያ ባለሙያዎች ጋር ተወያይተዋል።
ኤምባሲው ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በትብብር አዘጋጅቶት በነበረው የ"ፋሚሊያራይዜሽን" ጉብኝት ባለሙያዎቹ አንድነት፣ እንጦጦና ወዳጅነት ፓርኮችን እንዲሁም የወንጪ ዳንዲ ኢኮ ቱሪዝም መንደርን ጨምሮ የቱሪስት መዳረሻዎችን ተመልክተዋል።
ከጉብኝቱ መልስም ባለሙያዎቹ በኢትዮጵያ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን በተመለከተ በጂቡቲ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ በፈረንይኛ እና በሶሚልኛ ቋንቋዎች የተለያዩ ፕሮግራሞችን ማቅረባቸው ተገልጿል።
በተጨማሪም በጋዜጦች እና በማህበራዊ ድረ-ገጾች የኢትዮጵያን የቱሪስት መዳረሻዎች አስተዋውቀዋል።
አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ ከባለሙያዎቹ ጋር በነበራቸውም ቆይታ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ላከናወኑት መልካም ስራ ማመስገናቸውን ከኤምባሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ሁለቱ ወገኖች በቀጣይ ተመሳሳይ የኢትዮጵያ ልዑክ ጂቡቲን በሚጎበኝበት እና ሁለቱ አገራት በቱሪዝም ዘርፍ የጋራ ፓኬጆችን በማዘጋጀት በትብብር በሚሰሩበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውም ተገልጿል።