በተጠባቂው ጨዋታ ማንችስተር ዩናይትድ እና ቼልሲ ነጥብ ተጋርተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በተጠባቂው ጨዋታ ማንችስተር ዩናይትድ እና ቼልሲ ነጥብ ተጋርተዋል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 23/2017 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ10ኛ ሳምንት ተጠባቂ መርሃ ግብር ማንችስተር ዩናይትድ እና ቼልሲ አንድ አቻ ተለያይተዋል።
ማምሻውን በኦልድትራፎርድ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ የ30 ዓመቱ ፖርቹጋላዊ የአማካይ ተጫዋች ብሩኖ ፈርናንዴዝ በ70ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት ያስቆጠራት ግብ ማንችስተር ዩናይትድን መሪ አድርጎ ነበር። ተጫዋቹ በሊጉ የመጀመሪያ ጎሉን አስቆጥሯል።
ይሁንና የማንችስተር ዩናይትድ መሪነት የቆየው ለአራት ደቂቃ ብቻ ነበር።
የ23 ዓመቱ ኢኳዶራዊ የመሐል ሜዳ ተጫዋች ሞሰስ ካይሴዶ በ74ኛው ደቂቃ ከመረብ ላይ ያሳረፋት ግሩም ግብ ቼልሲን አድርጋለች። ካይሴዶ 23 ዓመት የሞላው ትናንት ነበር።
ሁለቱም ቡድኖች ጨዋታውን ማሸነፍ የሚችሉባቸውን የግብ እድሎች መጠቀም አልቻሉም።
ውጤቱን ተከትሎ ማንችስተር ዩናይትድ በ12 ነጥብ በነበረበት 13ኛ ደረጃ ላይ ረግቷል።
ቼልሲ በ18 ነጥብ ከነበረበት ስድስተኛ ደረጃ ወደ አራተኛ ከፍ ብሏል።
ቼልሲ ከእ.አ.አ ከ2013 አንስቶ ኦልድትራፎርድ ላይ ማንችስተር ዩናይትድን አሸንፎ አያውቅም።
ቀን ላይ በተደረገ ጨዋታ ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከመመራት ተነስቶ አስቶንቪላን 4 ለ 1 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል።
ሊቨርፑል በ25 ነጥብ ሊጉን እየመራ ይገኛል። ማንችስተር ሲቲ በ23 ነጥብ ይከተላል።
ኖቲንግሃም ፎረስት በ19 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። አርሰናል በ18 ነጥብ በቼልሲ በግብ ክፍያ ተበልጦ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።