በኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የተመራ ልዑክ ኤር ባስ ኤ350-1000 የአውሮፕላንን ለመረከብ ፈረንሳይ ገባ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የተመራ ልዑክ ኤር ባስ ኤ350-1000 የአውሮፕላንን ለመረከብ ፈረንሳይ ገባ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24/2017 (ኢዜአ)፡- የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥና ኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የተመራ ልዑክ ኤር ባስ ኤ350-1000 የመንገደኞች አውሮፕላንን ለመረከብ ፈረንሳይ ገብቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ አየር መንገዱ 124 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ማዘዙን መናገራቸው ይታወቃል።
ይህ ብቻ ሳይሆን አየር መንገዱ በዓመት እስከ 130 ሚሊየን መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችል ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩም እንዲሁ፡፡
ይህም የኢትዮጵያ አየር መንገድን በአፍሪካ ትልቁ የአውሮፕላን ባለቤት ብቻ ሳይሆን ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ያለው ተቋም ያደርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን ኤ350-1000 "Ethiopia land of origins" የተሰኘ የመንገደኞች አውሮፕላን ከኤር ባስ ኩባንያ በቅርቡ እንደሚረከብ ለኢዜአ መግለጹ ይታወሳል።
በዛሬው ዕለትም የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው እና ሌሎች የአየር መንገዱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አውሮፕላኑን ከኤር ባስ ኩባንያ ለመረከብ ፈረንሳይ ገብተዋል።
የኤር ባስ ኩባንያ ዋና መስሪያ ቤት የሚገኝበት ቱሉስ ከተማ ሲደርሱም የኤር ባስ ኩባንያ አመራሮች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኤ350-1000 አውሮፕላንን ወደ ገበያው ማስገባቱ አየር መንገዱ የያዘውን ፈጣን እድገት በላቀ ደረጃ ለማሳለጥ ትልቅ ትርጉም እንደሚኖረው ታምኖበታል።
በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኤር ባስ ኤ350-1000 የመንገደኞች አውሮፕላን በቀጣይ ሳምንት ማክሰኞ አዲስ አበባ ይገባል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዚህ ቀደም የኤ350-900 አውሮፕላኖችን ጨምሮ ሌሎች በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆኑ አውሮፕላኖችን ቀድሞ በማስገባት የሚታወቅ ነው።
አየር መንገዱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2035 በዓመት 67 ሚሊየን መንገደኞችን በማጓጓዝ 25 ቢሊየን ዶላር ዓመታዊ ገቢ ለማግኘት እየሰራ ነው።