የምርምር ሥራዎች ከችግር ፈቺነት ባለፈ በሀገራዊ እድገት ላይ ያላቸውን ሚና ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል--ሚኒስቴሩ

ዲላ ፤ጥቅምት 24/2017 (ኢዜአ)--በዩኒቨርሲቲዎች የሚከናወኑ የምርምር ሥራዎች የማህበረሰቡን ችግር ከመፍታት ባለፈ በሀገራዊ እድገት ላይ ያላቸውን ሚና ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። 

"የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ለሁለንተናዊ ዕድገት" በሚል መሪ ቃል የማህበረሰብ ጉድኝትና የኢንዱስትሪ ትስስር የውይይት መድረክ በዲላ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።


 

በትምህርት ሚኒስቴር የምርምርና የማህበረሰብ ጉድኝት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሠራዊት ሃንዲሶ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፣ የምርምር ሥራዎች የማህበረሰቡን ችግር ከመፍታት ባለፈ በሀገራዊ እድገት ላይ የሚኖራቸውን ሚና ለማሳደግ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው።

ተቋማቱ በተለይ በምርምርና በፈጠራ እንዲሁም በቴክኖሎጂ ልማት ያላቸውን አበርክቶ ለማሳደግና ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ ትኩረት መደረጉንም አንስተዋል።

በዩኒቨርሲቲ፣ ኢንዱስትሪና ማህበረሰቡ መካከል ያለውን ትስስር ማጠናከር ቀዳሚ አጀንዳ አድርጎ እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ለዚህም የተደራጀና ገበያ መር የሆነ የምርምር ሥርዓት መዘርጋቱን ዶክተር ሠራዊት ጠቁመው፣ ይህም የምርምር ሥራዎችን ለላቀ ሀገራዊ እድገት ለመጠቀም ያስችላል ብለዋል።

ያልተቀናጀ የቴክኖሎጂ አጠቃም ያሉንን የሰው ሀይልና የተፈጥሮ ጸጋ በአግባቡ አልምተን እንዳንጠቀም ማነቆ ነው ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ናቸው።


 

ቴክኖሎጂ አሰራር ከማዘመን ጀምሮ የተሻሻሉ ማሽነሪዎችን እስከመጠቀም የሚያደርስ የምርምር ውጤት መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም ምሁራን፣ ኢንዱስትሪውና ማህበረሰቡ ተቀናጀተን መስራት አለብን ብለዋል።

በተለይ ሀገር በቀል እውቀትና ባህልን ያቀናጀ የምርምር ሥራ በማከናወን ከሀገር ባለፈ አፍሪካንም ተጠቃሚ ለማድረግ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባም አመላክተዋል።

ዩኒቨርሲቲው በተግባር ተኮር የትኩረት መስክ መለየቱ ከማህበረሰቡና ከኢንዱስትሪ ጋር ተቀራርቦ በቅንጅት እንዲሰራ አቅም መፍጠሩን ያነሱት ደግሞ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኤልያስ አለሙ ናቸው።


 

በዚህም የአካባቢውን ማህበረሰብ የአኗኗር ሁኔታ የሚቀይሩና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን የሚያሳድጉ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎች ላይ ወጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ለሁለንተናዊ የማህበረሰብ እድገት ቁልፍ መሆኑን ጠቁመው፣ የማህበረሰቡን ችግር ለሚፈቱና እሴት ለሚጨምሩ ሥራዎች ትኩረት መሰጠቱን አመልክተዋል።

የዛሬው የውይይት መድረኩ በተቀናጀ መንገድ ለሚሰሩ ሥራዎች አቅም እንደሚፈጥርም ነው ያመለከቱት።


 

በጌዴኦ ዞን ቡና ላኪ አርሶ አደር ዳዊት ጅክሶ በበኩላቸው በግብርና ልማት በተለይም በቡና ልማት ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በቅርበት በመስራታቸው ውጤታማ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።

በተለይ በተሻሻሉ የግብርና አሰራሮች ላይ የተፈጠረላቸውን ግንዛቤን ተግባራዊ በማድረጋቸው ምርታማነትን ማሳደግ እንደቻሉም ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ቡና በሄክታር እስከ 19 ኩንታል መሰብሰባቸውንና ባለልዩ ጣዕም ቡና አዘጋጅተው ለውጭ ገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም