የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተሳታፊዎች የወከሏቸውን ህብረተሰብ ክፍሎች ሀሳብ በነፃነት ማንሳትና መወያየት አለባቸው -- የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተሳታፊዎች የወከሏቸውን ህብረተሰብ ክፍሎች ሀሳብ በነፃነት ማንሳትና መወያየት አለባቸው -- የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን
ቦንጋ፤ ጥቅምት 24/2017 (ኢዜአ) :- የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አጀንዳ ማሰበሳብ ሂደት ተሳታፊዎች የወከሏቸውን ህብረተሰብ ክፍሎች ሀሳብ በነፃነት ማንሳትና መወያየት አለባቸው ሲል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች አስገነዘቡ።
ኮሚሽኑ የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራውን ዛሬ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቦንጋ ከተማ አስጀምሯል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው፣ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የሚሳተፉ የህብረተሰብ ተወካዮች በመደማመጥና በነጻነት ማቅረብ አለባቸው ብለዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ የሁሉም ተሳታፊ ድምፅ የሚሰማበት፣ የመፍትሄ ሃሳቦች የሚደመጡበትና ሀገራዊ መግባባት የሚፈጠርበት መሆኑንም ጠቁመዋል።
ለምክክሩ መሳካት የህብረተሰብ ተወካዮች የወከሏቸውን የህብረተስብ ክፍሎች ሀሳብ በመደማመጥና በመከባበር መርህ እንዲያቀርቡ አስገንዝበዋል።
ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ በበኩላቸው በተለያየ ጊዜ ያጋጠሙ የሀሳብ ልዩነቶችንና አለመግባባቶች በንግግርና በመመካከር ለመፍታት የምክክር ሂደቱ ተሳታፊዎች የተጣለባቸውን ሀላፊነት መወጣት አለባቸው ብለዋል።
የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ለተከታታይ 7 ቀናት እንደሚያካሄድ አስታውሰዋል።
''ውስጣዊ ችግሮቻችንን በምክክር በማስወገድ ሰላሟና አንድነቷ የተጠበቀ ሀገርን ለትውልድ እናስተላልፋለን'' ያሉት ደግሞ ባህላዊ መሪ መሆናቸውን የተናገሩት ወልታታ ባህሩ ወልደጊዮርጊስ ናቸው።
ችግሮችን በመነጋገርና በውይይት በመፍታት የሀገር ሰላምና አንድነትን ለማምጣት ምክክሩ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው አንስተዋል።
ሌላዋ የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ አስቴር አሸናፊ፣ ከዚህ ቀደም እንዲህ አይነት ሀገራዊ ምክክር ባለመኖሩ ተቀራርቦ ከመነጋገር ይልቅ ችግሮችን በሀይል የመፍታት መንገዶች ይታዩ ነበር ብለዋል።
በሀገራዊ ምክክሩ ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት የሚያስችል ቁልፍ መሳሪያ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።