ቀጥታ፡

በሉሲ ሙዚየም ግንባታ ኘሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ ያተኮረ መድረክ በሠመራ ከተማ እየተካሄደ ነው

ሰመራ ፤ ጥቅምት 24/2017(ኢዜአ)፦ በሉሲ ሙዚየም ግንባታ ኘሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ እና በታችኛው አዋሽ ሸለቆ ዓለም አቀፍ ቅርስ ላይ የሚመክር የባለድርሻ አካላት መድረክ በሰመራ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የሉሲ ሙዚየም የግንባታ ፕሮጀክትን ለማከናወን የሚያስችል ስምምነት ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተመላክቷል።

ከሙዚየም ግንባታ ፕሮጀክቱ በተጨማሪ በአፋር ክልል የታችኛው አዋሽ ሸለቆ የአርኬዎሎጂካል እና ፓሊአንቶሎጂ መገኛ ሥፍራዎችን አስመልክቶ ሊከናወኑ በታሰቡ ሥራዎች ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው።


 

በመጀመሪያው ምዕራፍ የሉሲ ሙዚየም ግንባታ ፕሮጀክትና ሙዚየሙ በሚገነባበት ቦታ ፕላን ላይ በትኩረት እንደሚመከርም ታውቋል።

ለሉሲ ሙዚየም ግንባታ የተዘጋጀውን ፕላን ከማጸደቅ በተጨማሪ "አደአር፣ ጎና እና ዲካካ" ለተሰኙ ሦስት ሥፍራዎች በተዘጋጀ ዲጅታል ካርታ ላይ ውይይት ይደረጋል።

ለስፍራዎቹ ዲጂታል ካርታ የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ከስፔስ ሳይንስና ጂኦስፖሻል ኢንስቲቲዮት ጋር በመተባበር መሆኑንም ተመላክቷል።

ሦስቱ ሥፍራዎች የዓለም ዓቀፍ ቅርስ ዋነኛ መገኛ በመሆናቸው ለጥናትና ምርምር፣ ለጥበቃ፣ ለአስተዳደር፣ ለህብረተሰብ ተጠቃሚነት ያመቸ ካርታ እንዲዘጋጅላቸው መሆኑን ተገልጿል።

በመድረኩ ላይ ከአፋር ክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ፣ ከመሬት አስተዳደር ቢሮ፣ ከአደአር ወረዳ የተለያዮ ማህበረሰብ ተወካዮች፣ ከኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ፅህፈት ቤትና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ጌታቸው ሮቤራ፣ የቅርስ አስተዳደር መሪ ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ፀሐይ ካሣ እና የአፋር ክልል ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ኢብራሂም ሁመድ እንዲሁም የመሬት አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ተገኝተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም