በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በትምህርት ዘርፍ ውጤት ለማስመዝገብ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በትምህርት ዘርፍ ውጤት ለማስመዝገብ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው
ወልቂጤ ፡ ጥቅምት 24/2017(ኢዜአ):- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በትምህርት ዘርፍ ያጋጠሙ ችግሮችን በመፍታት ተጨባጭ ውጤት ለማስመዝገብ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የጉራጌ ዞን ትምህርት ዘርፍ ጉባኤ በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አስከብር ወልዴ እንዳሉት፣ በክልሉ በትምህርት ዘርፍ ያሉ ማነቆዎችን በመፍታት ውጤት ለማስመዝገብ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው።
በተለይም የትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሻሻል፣ የማስተማሪያ የግብዓት ማሟላት፣ የመምህራን አቅም ማሳደግ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
የትምህርት ቤት አመራር ሪፎርም እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው ወላጆችና መምህራን እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለዚህ ስኬት እያደረጉት ያለው ተሳትፎ የሚበረታታ መሆኑንም አብራርተዋል።
የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማርያም በበኩላቸው፣ በዞኑ ከደረጃ በታች የሆኑ ትምህርት ቤቶችን የማሻሸል ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በዞኑ በ2016 የትምህርት ዘመን ከ493 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በማሰባሰብ ከ421 በላይ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻልና በአዲስ መልክ የመገንባት ሥራ መከናወኑንም አስረድተዋል።
የመፅሀፍት እጥረት፣ የመምህራንና የወላጆች ቅንጅት ያለመጠናከርና ችግሮች እንዳሉ ጠቅሰው እነዚህን ለማረም ተግተን እንሰራለን ሲሉ ገልጸዋል።
ከጉባኤው ተሳታፊዎች መካከል የእምድብር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ግንባሩ በርጋ እንደገለፁት፣ በከተማው የቅድመ አንደኛና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደረጃ ለማሻሻል ህዝብን ያሳተፈ ስራ እየተሰራ ነው።
በዚህም በተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል ላይ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት ለቅንጅታዊ አሰራር ትኩረት መሰጠቱንም ተናግረዋል።
በመድረኩ ከተሳተፉ የተማሪ ወላጆች መካከል አቶ ገረመው ቸገን፣ ለተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል በምክንያትነት የሚጠቀሱ ችግሮችን ፈጥኖ ለመለየት የተደረገው ጥረት መልካም መሆኑን አንስተው መፍትሔ ለመስጠት የሚደረጉ ጥረቶችን እናግዛለን ብለዋል።
በጉባኤው ላይ በሀገር አቀፍና ክልል አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ሽልማትና በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ መርሐ ግብር አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና ተሰጥቷል።