የአዋሽ መልካሳ ኬሚካል ፋብሪካ የኬሚካል ምርቶቹን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል አቅም መፍጠሩን ገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
የአዋሽ መልካሳ ኬሚካል ፋብሪካ የኬሚካል ምርቶቹን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል አቅም መፍጠሩን ገለፀ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24/2017(ኢዜአ)፦ የአዋሽ መልካሳ ኬሚካል ፋብሪካ የሚያመርታቸውን ኬሚካሎች ከአገር ውስጥ በተጨማሪ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል አቅም መፍጠሩን አስታወቀ።
የፋብሪካው ዋና ስራ አስኪያጅ አህመድ ሞቱማ ለኢዜአ እንዳሉት ፋብሪካው ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆኑ መሰረታዊ ኬሚካል የሚባሉትን ሰልፈሪክ አሲድ፣ አሉሚኒየም ሰልፌትና ሀይድሮጂን ፐርኦክሳይድ እያመረተ ይገኛል።
ፋብሪካው ከ1987 ጀምሮ ሁለቱን ምርቶች እያመረተ መቆየቱንና ከ2009 ጀምሮ ደግሞ ሀይድሮጂን ፐርኦክሳይድ እያመረተ እንደሆነ ገልፀዋል።
ፋብሪካው እነዚህን ኬሚካሎች እያመረተ ለአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም ሀይድሮጂን ፐርኦክሳይድን ለጎረቤት አገራት ገበያ ሲያቀርብ መቆየቱን ተናግረዋል።
ድርጅቱ በገጠሙት ችግሮች ሳቢያ በሙሉ አቅሙ አለመንቀሳቀሱን አስታውሰው መንግስት በሰጠው ትኩረት ችግሮቹን በመፍታት ለአገር ውስጥና ውጭ ገበያ የሚውል ምርት እያመረተ ነው ብለዋል።
ምርቶቹን ከአገር ውስጥ ገበያ በተጨማሪ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል አቅም መፈጠሩንም ገልፀዋል።
በዚህም ከውጭ የሚመጣውን በመተካት ለአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች አስተማማኝ ግብዓት አቅራቢ ለመሆንና ወደሌሎች አገራትም ለመላክ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ስለሆነም ቀደም ሲል ሲያቀርብባቸው የነበሩ የጎረቤት አገራት ገበያን ጨምሮ ወደሌሎች የውጭ አገራት የኬሚካል ምርቱን ለማቅረብ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመሆን እየሰራ እንደሆነም አስረድተዋል።
ለሚያመርታቸው ምርቶች የሚውሉ ግብዓቶችን በአገር ውስጥ ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።