ቀጥታ፡

የምክክር መድረኩ በችግሮቻችን ላይ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ለመነጋገር ዕድል ሰጥቶናል-የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች

ሶዶ፤ጥቅምት 24/ 2017 (ኢዜአ)፡-የምክክር መድረኩ በችግሮቻችን ላይ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በነጻነት ለመነጋገር ዕድል ሰጥቶናል ሲሉ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ፣የሀይማኖት ተቋማትና የማህበረሰብ ተወካዮች ገለጹ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሀገራዊ የምክክር ከተለያዩ የማህበረሰብ ተወካዮች አጀንዳ ለማሰባሰብ ያለመ መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማኔጂንግ ዳይሬክተርና በምክክር መድረኩ ዩኒቨርሲቲውን ወክለው የተገኙት አቶ ወርቅአገኘሁ በፍቃዱ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የምክክር ሂደቱ አካታች፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን ተናግረዋል።

የምክክር መድረኩ በህዝብና በመንግሥት መካከል መተማመንን የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመው፣በመድረኩ የህብረተሰቡ ችግሮች በነጻነት ተነስተው ሲንሸራሸሩ እንደነበር ገልጸዋል።

የተለያዩ የህብረተስብ ክፍሎች በጋራ መምከራቸው የህዝብን መፃኢ እድልና ተስፋ እንደሚያለመልም ገልጸው፣እስከዛሬ ተቀራርቦ የመነጋገር ዕድል ባለመኖሩ ጥቃቅን ጉዳዮችና የሀሰት ትርክቶች ለንትርክ ምክንያት ሲሆኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

የታጠቁ አካላትም ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ሊዘጋጁ ይገባል ያሉት አቶ ወርቅአገኘሁ፣በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ ችግሮችን በንግግር በመፍታት ልዩነትን ማጥበብና ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባም መክረዋል።

ቁጭ ብለን መመካከር ባለመቻላችን ችግሮችን በሀይል ለመፍታት ስንጥር እንታያለን" ያሉት ደግሞ የወላይታ ዞን የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት ድጋፍና ልማት ማህበር ሰብሳቢና በምክክር መድረኩ የማህበሩ ተወካይ መቶ አለቃ ማሜ ጫመና ናቸው።


 

ችግሮችን በመሳሪያ ለመፍታት የሄድንበት መንገድ ከጥፋት በቀር አንዳች ጥቅም አላስገኘልንም፣ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ ተነጋግሮ መፍታት ትርፋማና አዋጭ መንገድ ነው ብለዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች ችግሮችን በሀይል ለመፍታት እየተንቀሳቀሱ ያሉ አካላት ራሳቸውን ለውይይት ማዘጋጀት እንዳለባቸው አንስተው፥ሁሌም ከራስ ፍላጎት በላይ ሀገርን ማስቀደም ይገባል ብለዋል።


 

የወላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ወህዲግ) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊና የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ተመስገን ቶራ የምክክር ሂደቱ አካታች፣ፍትሃዊ እና ገለልተኛ መሆኑን መገንዘባቸውን ገልፀው፥በዚህ ታሪካዊ ሁነት በመሳተፋቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመድረኩ ሁሉም ተሳታፊ ሀሳቡን በነጻነትና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ሲያንሸራሽር እንደነበር ገልጸው፥ በምክክሩ መሳተፍ ያለባቸውን ሁሉ ለማካተት የተጀመረው ጥረት መጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ስነጽሑፍ መምህርትና የጌዴኦ ዞን አካል ጉዳተኞች ማህበር ሰብሳቢ መምህርት ፍቅርተ መኮንን አካል ጉዳተኞች ትኩረት ከተነፈጋቸው የማህበረሰብ ክፍሎች አንዱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።


 

ይህም ትልቅ ቁጭት ሲፈጥርባቸው እንደነበር አንስተው በምክክር መድረኩ እንዲሳተፉ በመደረጉ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የምክክር መድረኩ ዘላቂ መፍትሄ የሚገኝበት እንደሆነ እረዳለሁ ያሉት ደግሞ የጌዴኦ ዞን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ሰብሳቢና የምክር ቤቱ ተወካይ ኡስታዝ አብዱረህማን አብዱቁ ናቸው።

የምክክር ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆን መንግስትን ጨምሮ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል።


 

በሀገራዊ ምክክሩ የጋራ መግባባት የተደረሰባቸው ሀሳቦች በአፅንኦት መታየት እንዳለባቸው አንስተው፥መንግስትም በምክክሩ ለሚነሱ የህዝብ አጀንዳዎች ተገቢ ትኩረት መስጠት እንደሚኖርበትም አመልክተዋል።

በክልሉ ለቀናት ሲካሄድ የቆየው አጀንዳ የማሰባሰብ መድረክ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የምክክር መድረክ ክልሉን ወክለው የሚሳተፉ ተወካዮችን በመምረጥ ዛሬ ከሰዓት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም