በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው ኤር ባስ ኤ350-1000 የመንገደኞች አውሮፕላን በቀጣይ ሳምንት ማክሰኞ አዲስ አበባ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው ኤር ባስ ኤ350-1000 የመንገደኞች አውሮፕላን በቀጣይ ሳምንት ማክሰኞ አዲስ አበባ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24/2017(ኢዜአ)፦ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኤር ባስ ኤ350-1000 የመንገደኞች አውሮፕላን በቀጣይ ሳምንት ማክሰኞ አዲስ አበባ ይገባል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ አየር መንገዱ 124 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ማዘዙን መናገራቸው ይታወቃል፡፡
ይህ ብቻ ሳይሆን አየር መንገዱ በዓመት እስከ 130 ሚሊየን መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችል ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩም እንዲሁ፡፡
ይህም የኢትዮጵያ አየር መንገድን በአፍሪካ ትልቁ የአውሮፕላን ባለቤት ብቻ ሳይሆን ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ያለው ተቋም ያደርገዋል፡፡
አየር መንገዱ እያስመዘገበ ያለው ስኬት የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ማሳያ ሲሆን፤ በበጀት ዓመቱ በአገልግሎት ዘርፍ 7 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ለማስመዝገብ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ሚናው የጎላ ነው፡፡
የአየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ዋና ኃላፊ ለማ ያዴቻ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ በአፍሪካ የአቪዬሽን መስክ ያለውን የቀዳሚነት ድርሻውን ለማስቀጠል በየጊዜው አዳዲስ አውሮፕላኖችን በማስመጣት ላይ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም አየር መንገዱ ከኤር ባስ ኩባንያ የገዛውና በአፍሪካ የመጀመሪያው የሆነው ኤ350-1000 ዘመናዊ አውሮፕላን በቀጣይ ሳምንት ማክሰኞ ወደ አዲስ አበባ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በአቪዬሽን ዘርፍ ውድድሮች እየጠነከሩ መምጣታቸውን ጠቅሰው፤ እነዚህን ውድድሮች ማሸነፍ የሚቻለው ጊዜውን የዋጀ የበረራ አውሮፕላን በመጠቀም ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድም ይህን ከግንዛቤ በማስገባት ዘመናዊ የሆነውን ኤ350-1000 የመንገደኞች አውሮፕላን መግዛቱን ተናግረዋል።
አውሮፕላኑ ለመንገደኞች ምቹ የሆኑ እጅግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙለትና የነዳጅ ፍጆታ ዝቅተኛ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አውሮፕላኑ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አቪዬሽን ዘርፍ ያላትን ግንባር ቀደም ሚና የሚያረጋግጥ እንደሆነ ተናግረዋል።
አየር መንገዱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2035 በዓመት 67 ሚሊየን መንገደኞችን በማጓጓዝ 25 ቢሊየን ዶላር ዓመታዊ ገቢ ለማግኘት እየሰራ ነው።
በአሁኑ ወቅትም ባሉት 147 አውሮፕላኖች 139 ዓለም አቀፍና 22 የሀገር ውስጥ የበረራ መዳረሻዎችን እየሸፈነ ይገኛል።