በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ በማንችስተር ዩናይትድ እና ቼልሲ መካከል ይደረጋል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24/2017 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ10ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ማንችስተር ዩናይትድ እና ቼልሲ ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከምሽቱ 1 ሰዓት ከ30 74 ሺህ 310 ተመልካች በሚያስተናግደው ኦልድ ትራፎርድ ስታዲየም ይደረጋል።

ማንችስተር ዩናይትድ እና ቼልሲ በሁሉም ውድድሮች ሲገናኙ የአሁኑ 196ኛ ጊዜ ነው ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም 195 ጊዜ ተጫውተው ማንችስተር ዩናይትድ 83 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። ቼልሲ 56 ጊዜ ድል ቀንቶታል።

56 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

ማንችስተር ዩናይትድ በዘንድሮው የውድድር ዓመት እስከ አሁን ባደረጋቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ አራት ጊዜ ተሸንፏል። ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል። 

ቡድኑ በጨዋታዎቹ 8 ግቦችን ሲያስቆጥር 11 ግቦችን አስተናግዷል።

ማንችስተር ዩናይትድ በ11 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ተጋጣሚው ቼልሲ በበኩሉ በሊጉ ባካሄዳቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች አምስት ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። በሁለቱ ነጥብ ተጋርቷል። 

ቡድኑ በጨዋታዎቹ 19 ግቦችን ሲያስቆጥር 11 ጎሎች ተቆጥረውበታል። ቼልሲ በ17 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ማንችስተር ዩናይትድ በዘጠነኛው ሳምንት መርሃ ግብር በዌስትሃም ዩናይትድ 2 ለ 1 ከተሸነፈ በኋላ የ54 ዓመቱን አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግን አሰናብቷል።

የ48 ዓመቱ ኔዘርላንዳዊ የቀድሞ የክለቡ ተጫዋች ሩድ ቫኒስትሮይ በጊዜያዊ አሰልጣኝነት በማገልገል ላይ ናቸው።

ይሁንና የ39 ዓመቱ ፖርቹጋላዊ የስፖርቲንግ ሊዝበን አሰልጣኝ የነበሩትን ሩበን አሞሪም አዲሱ የማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሆነው ተሾመዋል። እ.አ.አ እስከ 2027 የሚያቆያቸውን ውል ፈርመዋል።

አሞሪም በ12ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር ማንችስተር ዩናይትድ ከኢፕሲዊች ታውን በሚያደርገው ጨዋታ በይፋ ስራቸውን ይጀምራሉ።

ጊዜያዊ አሰልጣኙ ሩድ ቫኒስትሮይ በሳምንቱ አጋማሽ ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ድል ቀንቶታል። 

ረቡዕ በካራባኦ ካፕ የአራተኛ ዙር መርሃ ግብር ኦልትራፎርድ ላይ በተደረገ ጨዋታ ማንችስተር ዩናይትድ ሌይስተር ሲቲን 5 ለ 2 አሸንፏል።

ቫኒስትሮይ ከቼልሲ ዛሬ ጠንካራ ፈተና ይጠብቀናል፣ በአንድነት እና በጥንካሬ መንፈስ ጨዋታውን ለማሸነፍ እንጫወታለን ሲል ገልጿል።

ቡድኑ ሌይስተርን ሲያሸንፍ ያሳየውን ብቃት እና መነሳሳት በዛሬው ጨዋታ ለመድገም ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።

የ44 ዓመቱ ጣልያናዊ የቼልሲ አሰልጣኝ ኢንዞ ማሬስካ በዛሬው ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ይጠብቀናል፣ ኦልድትራፎርድ ለየትኛውም ክለብ ጨዋታን ለማሸነፍ የሚከብድ ስታዲየም መሆኑን ገልጿል።

ቼልሲ ከእ.አ.አ 2013 በኋላ በኦልትራፎርድ አሸንፎ አያውቅም ያንን ታሪክ ለመቀየር ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው ብሏል።

የ37 ዓመቱ ሮበርት ጆንስ የሁለቱን ቡድኖች ተጠባቂ ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

በተያያዘም ትናንት በተደረጉ የ10ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ሊቨርፑል ብራይተን ኤንድ ኦቭ አልቢዮንን 2 ለ 1 አሸንፏል። ውጤቱን ተከትሎ በ25 ነጥብ የሊጉን መሪነት ከማንችስተር ሲቲ ተረክቧል።

ማንችስተር ሲቲ በቦርንማውዝ 2 ለ 1 እንዲሁም አርሰናል በኒውካስትል ዩናይትድ 1 ለ 0 ተሸንፈዋል።

ማንችስተር ሲቲ በ23 ነጥብ ሁለተኛ፣ አርሰናል በ18 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዘዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም