ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24/2017 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሰባተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል።

ባህር ዳር ከተማ ከወላይታ ድቻ ከቀኑ 10 ሰዓት በድሬዳዋ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የሚመራው ባህር ዳር ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ሶስቱ ጊዜ ተሸንፏል። 

በጨዋታዎቹ አምስት ግቦችን ሲያስቆጥር ሶስት ጎሎችን አስተናግዷል። ባህር ዳር ከተማ በዘጠኝ ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ተጋጣሚው ወላይታ ድቻ አሁን በሊጉ ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች  አራቱን ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ሽንፈትን አስተናግዷል። ቡድኑ ዘጠኝ ጎሎችን ሲያስቆጥር 10 ግቦች ተቆጥረውበታል።

በያሬድ ገመቹ የሚሰለጥነው ወላይታ ድቻ በ12 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። 

የሰባተኛ ሳምንት ሁለተኛ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አርባምንጭ ከተማ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ያገናኛል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊጉ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች መካከል ሁለቱን ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ሽንፈት ገጥሞታል።

በጨዋታዎቹ ስድስት ግቦችን ሲያስቆጥር ስድስት ጎሎች ተቆጥረውበታል።

በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመራው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሰባት ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ተጋጣሚው አርባምንጭ ከተማ እስከ አሁን በሊጉ ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ  በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪው አንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርቷል።

በአምስቱ ጨዋታዎች አራት ግቦችን ሲያስቆጥር አምስት ጎሎችን አስተናግዷል።

በበረከት ደሙ የሚመራው አርባምንጭ ከተማ በሰባት ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል።

የሊጉ መርሃ ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል መቻል ከአዳማ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት፣ ኢትዮጵያ መድን ከመቀሌ 70 እንደርታ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ሃዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡና የሰባተኛ ሳምንት አራፊ ቡድኖች ናቸው።

ሲዳማ ቡና ሊጉን በ12 ነጥብ እየመራ ይገኛል።

የመቀሌ 70 እንደርታው አጥቂ ያሬድ ብርሃኑ በአምስት ግቦች የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት እየመራ ይገኛል።

ዩጋንዳዊው የድሬዳዋ ከተማ አጥቂ ቻርልስ ሙሲጌ እና ሌላኛው የቡድኑ የፊት መስመር ተሰላፊ መሐመድ ኑር ናስር እንዲሁም የወላይታ ድቻው አጥቂ ያሬድ ዳርዛ በተመሳሳይ በአራት ግቦች ይከተላሉ።

የሰባተኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ጥቅምት 27 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆይ የሊጉ አክሲዮን ማህበር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም