ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ባንግላዴሽ ዳካ ከተማ በረራ ጀመረ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 23/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ባንግላዴሽ ዳካ ከተማ በረራ ጀመረ ።

አየር መንገዱ ወደ ዳካ ከተማ በሣምንት አምስት ጊዜ በረራ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

አየር መንገዱ ወደ ባንግላዴሽ ዳካ ከተማ የሚያደርገውን በረራ አስመልከቶ ዛሬ ማምሻውን የማስጀመሪያ መርኃ ግብር ተከናውኗል። 

በመርኃ ግብሩ የአየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ዋና ኃላፊ ለማ ያዴቻ፣ በኢትዮጵያ ባንግላዴሽ አምባሳደር  ሲክደር ቦዲሩዛማን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። 

የአየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ዋና ኃላፊ ለማ ያዴቻ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት አየር  መንገዱ በደቡብ ኤስያ የሚያደርገውን የበረራ አገልግሎት በማሳደግና የሁለቱን አገራት ሕዝቦች በማቀራረብ ረገድ በረራው ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል። 


 

በረራው የደቡብ ኤሲያ ገበያን ተደራሽ በመሆን አቅም የሚፈጥር መሆኑንም ጠቁመዋል። 

አየር መንገዱ አዳዲስ አውሮፕላኖችን ወደ ገበያው በማስገባት የበረራ ተደራሽነቱን እያሳደገ መሆኑን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ባንግላዴሽ አምባሳደር ሲክደር ቦዲሩዛማን በበኩላቸው አየር መንገዱ ወደ ዳካ የሚያደርገው በረራ የሁለቱን አገራት ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም