በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የዓለም አቀፍ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ዋንጫ አህጉራዊ ሻምፒዮና ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የዓለም አቀፍ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ዋንጫ አህጉራዊ ሻምፒዮና ተጀመረ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 23/2017(ኢዜአ)፡- የዓለም እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ዋንጫ አህጉራዊ ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና (IHF Trophy Africa) ዛሬ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ተጀምሯል።
በሻምፒዮናው መክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ የባህል ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ እና የሚኒስቴሩ ከፍተኛ አመራሮች፣የአፍሪካ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ማዳት መሐመድ አሕመድ፣ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አንበሳው እንየው እና የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፍትሕ ወልደሰንበት ተገኝተዋል።
እጅ ኳስ ኢትዮጵያ ውስጥ እያደገና ውጤት እያመጣ ያለ ስፖርት ነው፤ ከዚህ የበለጠ ስፖርቱን ለማሳደግ ድጋፍና ክትትል እንደሚፈልግ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
መንግስት የእጅ ኳስን ጨምሮ ሌሎች ስፖርቶች እንዲስፋፋና ውጤት እንዲያመጡ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።
የአፍሪካ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ኢትዮጵያ ሻምፒዮናውን እንድታዘጋጅ በመምረጡ መስጋና ያቀረቡት ሚኒስትሩ ስፖርቱ በአህጉር አቀፍ ደረጃ እንዲያድግ ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።
“ስፖርት ለአህጉራዊ ሰላም” “ በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደውን ሻምፒዮና የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ከዓለም አቀፉ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን እና ከአፍሪካ እጅ ኳስ ኮንፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ነው።
ኢትዮጵያ፣ ጊኒ፣ ማዳጋስካር፣ ካሜሮን፣ ናይጄሪያ እና ዛምቢያ በወጣቶች ከ18 ዓመት በታች ይወዳደራሉ።
ኮንጎ ሪፐብሊክ ፣ጋና፣ ጊኒ፣ ሩዋንዳ እና ዚምባብዌ ከ20 አመት በታች የሚወዳደሩ አገራት ናቸው።
ሻምፒዮናው እስከ ጥቅምት 27 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ ከባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።