ህዳሴ - በመስዋዕትነት የተገነባ ነገ - ኢዜአ አማርኛ
ህዳሴ - በመስዋዕትነት የተገነባ ነገ
ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ከፕሮጀክት ባለፈ የኢትዮጵያውያን በጋራ የመቻል ትምህርት ነው።
የወል ዕውነታቸው፣ የወል አቅማቸው፣ የጋራ ተስፋቸው በግልጽ የተንጸባረቀበት የአይበገሬነት ምልክት ጭምር ነው።
ኢትዮጵያውያን ነጋቸውን እንዴት በጋራ መገንባት እንደሚችሉ በሚገባ ያሳዩበት ዳግማዊ አድዋ ነው - ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ።
አድዋ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ለነጻነት የተዋደቁበት ደማቅ የታሪክ ምዕራፍ ሲሆን ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ደግሞ ለኢኮኖሚ ሉአላዊነት የደም ዋጋ የተከፈለበት የትውልዱ የብሄራዊነት ማሳያ ነው።
ህዳሴን ዕውን ለማድረግ ኢትዮጵያ ከሴራ ዘመቻዎች እስከ ዛቻና ማስፈራሪያዎች የደረሱ እንቅፋቶችን አልፋለች።
በተለይም የግድቡ ግንባታ ወደማይቀበለስበት ደረጃ በደረሰባቸው ያለፉት 6 ዓመታት ፈተናዎቹ በርትተው ነበር።
ለህዳሴው ግድብ ግንባታ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ተጓጉዘው እንዳይደርሱ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ምርት እንዳያመርቱና እንዳያቀርቡ በተለየዩ ቦታዎች ጥቃቶች ይሰነዘሩ ነበር።
ቢሆንም ግን የማያባሩ የኢትዮጵያ ጠላቶችን የተንኮል ወጥመዶች በጣጥሶ ለማለፍ ኢትዮጵያውያን አይተኬ ህይወታቸውን ጭምር ገብረው ነገን ዛሬ መስራትን በህዳሴ ዕውን አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሕዳሴ ግድብ አሁን የደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ በርካታ መስዋዕትነት መከፈሉን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ሁሌም በጋራ የመልማት እሳቤ ማዕከል መሆኗን ገልጸው፤ታላቁ ህዳሴ ግድብም በኢትዮጵያዊያን ብርቱ ልጆች ከአፍሪካ ለአፍሪካ የተሰጠ ገጸ በረከት እንዲሁም ጣፋጭ ፍሬውም ከኢትዮጵያ ባለፈ ለተፋሰሱ አገራትም ብስራት መሆኑን ነው ያስረዱት።
የታላቁ የኢትዮጵየ ህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ አኩሪ ደረጃ ላይ ለመድረስ ኢትዮጵያውያን ከገንዘብ፣ ጉልበትና እውቀታቸው ባሻገር የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉበት ፕሮጀክት መሆኑን ጠቁመዋል።