ቀጥታ፡

ሕዝብን ያሳተፈ የልማት ተግባራትን በማከናወን በምግብ ራስን ከመቻል ያለፈ ምርት ማምረት ላይ በትኩረት እንሰራለን

ሚዛን አማን ፤ ጥቅምት 23/2017(ኢዜአ)፦ሕዝብን ያሳተፈ የልማት ተግባራትን በማከናወን በምግብ ራስን ከመቻል ያለፈ ምርት በማምረት ሃብትን መፍጠር ላይ በማተኮር እንደሚሠሩ የቤንች ሸኮ ዞን አመራሮች ገለጹ።

በምግብ ራስን መቻል የሕልውና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም ጓሮውን እንዲያለማ ሠርተን እናሠራለን ሲሉም ተናግረዋል።

ለኢዜአ ሀሳባቸውን ካጋሩ አመራር አባላት መካከል አቶ ሀብታሙ አላሎ እንዳሉት፤ ከዚህ ቀደም አጠገባችን ያሉ ምቹ የመልማት ዕድሎችን ባለመመልከታችን ምክንያት በሚጠበቀው ልክ ማደግ አልቻልንም።

አሁን ላይ ከለውጥ አስተሳሰብና በቂ የሰው ኃይል፣ ያልተነካ የእርሻ መሬትና ውሃ ያለን በመሆኑ "በምግብ ራስን ከመቻል ያለፈ ምርት ማምረት ይጠበቅብናል" ብለዋል።

ለዚህም ሕዝብን ያሳተፈ እንቅስቃሴ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን በኅብረተሰብ ተሳትፎ ለማቀላጠፍ በትኩረት እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በዞኑ ድልድዮችን፣ መንገዶችንና የስፖርት ማዘውተሪያ ስታዲየሞችን ለመገንባት እየተደረገ ያለው ሕዝባዊ ተሳትፎ ከተጠናከረ ዞኑ በቅርብ ጊዜ ውስጥ አዎንታዊ ለውጥ ያስመዘግባል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ዞኑ ያለው የተፈጥሮ ሀብት ጥቂት እሴት የሚጨመርበት ከሆነ ለሀገር የሚተርፍ የግብርና ምርት ያለበት አካባቢ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላዋ አመራር አባል ወይዘሮ ትዕግሥት ለማ ናቸው።


 

ያለንን ምቹ ሁኔታ በማስተዋል ሁላችንም ተባብረን ከሠራን ማደግና አካባቢያችንን መለወጥ እንችላለን ሲሉ ገልጸዋል።

አቶ ስንታየሁ ጋይድ የተባሉ አመራር በበኩላቸው በምግብ ራስን መቻል ለነገ የማይባል ጉዳይ መሆኑን በመንገንዘብ በስንዴ ልማት፣ በሌማት ትሩፋትና ምግቤን ከጓሮዬ በሚሉ ሀሳቦች ላይ ተመርቶ መሥራት ይገባል ብለዋል።


 

ለመልማት ማደግ ሩቅ ማማተር ሳይሆን ጓሮን መመልከት ብቻ በቂ እንደሆነ ገልጸው ከሕዝባችን ጎን ቆመን ሠርቶ በማሠራት ባህል ለለውጥ እንተጋለን ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም