ቀጥታ፡

ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ሀገራዊ ተልዕኮውን በብቃት ከመወጣት በተጓዳኝ በልማቱም ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል

ጋምቤላ፤ ጥቅምት 23/2017(ኢዜአ)፡- ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ሀገራዊ ተልዕኮውን በብቃት ከመወጣት በተጓዳኝ በተለያዩ ልማቶች ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ተገለጸ።

የጋምቤላ ክልል ከፍተኛ አመራር አባላትና የመከላከያ ሰራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖች ሰራዊቱ በክልሉ እያለማ ያለውን የእርሻ ስራ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ በጉብኝቱ ወቅት ፤ ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ሀገራዊ ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ የሚገኝ የሀገር አለኝታ ነው ብለዋል።

ከዚህም ጎን ለጎን በተለያዩ ልማቶች ላይ በመሰማራት የምግብ ዋስትናቸውን በራስ አቅም ለማረጋገጥ እየተካሄደ ባለው ስራም ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ መሆኑን አስታውቀዋል።


 

ሰራዊቱ የክልሉን ሰላም ከማስጠበቅ በተጨማሪ እያከናውኗቸው ያሉት የግብርና ልማት ስራዎች ለሌሎች ተቋማት ትልቅ መነሳሳትን የሚፈጥር እንደሆነም አብራርተዋል።

በጋምቤላ ክልል ያሉትን የልማት አቅሞች በሙሉ አስተባብሮ ወደ ውጤት ለመለወጥ መንግስት ከሁሉም አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ሰራዊቱ በክልሉ ለሚያከናውናቸው ማንኛውም የልማት ስራዎች የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንዲያደርግ አረጋግጠዋል።

የመከላከያ መሐንዲስ ዋና መምሪያ ሀላፊ ሌተናል ጄኔራል ደስታ አብቼ በበኩላቸው፤ ዋና መምሪያው ለሰራዊቱ መሠረተ ልማቶችን ከማሟላት ባለፈ የሰራዊቱን ህይወት ለማሻሻል በመላ ሀገሪቱ በግብርና ስራዎች ላይ መሰማራቱን ተናግረዋል።


 

ከዚህ ውስጥ በጋምቤላ ክልል አቦቦ ወረዳ በ156 ሄክታር መሬት ላይ የማሽላና የሰሊጥ ሰብል እያለማ ያለውን ጠቅሰዋል።

ሰራዊቱ በክልሉ የጀመረውን የልማት ስራዎች በቀጣይም ከክልሉ መንግስት ጋር በመተባበር የበለጠ ለማስፋፋት ዕቅድ መያዙንም ሌተናል ጀነራሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም