ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት ለማስከበር ሁለንተናዊ ብሔራዊ አቅም እየገነባን ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 23/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት ለማስከበር ሁለንተናዊ ብሔራዊ አቅም እየገነባን ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።

ብሔራዊ ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ በማስተርስ መርኃ ግብር ያሰለጠናቸውን የመረጃና ደኅንነት መኮንንና አመራሮችን አስመርቋል።

በምረቃ መርሐግብሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር የአንድን ሀገር ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት ማስከበር የሚቻለው ሁለንተናዊ ብሔራዊ አቅምን በመገንባት ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።

ሁለንተናዊ ብሔራዊ አቅም የወታደራዊ፣ የኢኮኖሚ፣ የዲፕሎማሲ፣ የመሰረተ-ልማት እና የኢንፎርሜሽን አቅሞችን የሚያጠቃልል ነው ብለዋል።

በመረጃ የበላይነት የያዘ ኃይልና ሀገር በሌሎች ሁኔታዎች ላይ የበላይነት የመያዝና የማሸነፍ እድሉ ሰፊ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

በዚህ ከፍተኛ ትግል የሚደረገው የመረጃ የበላይነት ለመያዝ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ መረጃ ትክክለኛ ውሳኔዎችን ለማሳለፍና በዘላቂነት ሀገርን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስትራቴጂክ እውቀት ነው ብለዋል።

ብሔራዊ ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ በመረጃው ዘርፍ እውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት የተላበሱ ዜጎችን ለማፍራት ትልቅ የአቅም ግንባታ ማዕከል መሆኑንም ተናግረዋል።

መንግሥት የመረጃን አቅምና ጥቅም በአግባቡ በመገንዘብ በደኅንነት ዘርፉ ላይ ስር ነቀል ሪፎርም ማካሄዱን ገልጸዋል።

የዛሬው ተመራቂዎችም በፈጣን የሀገራዊ፣ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ የደኅንነት ምህዳር ለወጥ ውስጥ ብሔራዊ ጥቅምንና ደኅንነትን በአስተማማኝ ሁኔታ ማስከበርን ዓላማ ያደረጉ ናቸው ብለዋል።


 

ይህም ብሔራዊ ጥቅምንና ደኅንነትን ለማስከበር አስፈላጊ የሆነውን ሰፊና ጥልቅ እውቀት እየተገነባ እንደሚገኝ የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የመረጃ ማህበረሰቡም የእውቀት ማህበረሰብ መሆን የሚችለው በአስፈላጊና ዘመኑን በዋጀ ትምህርትና ስልጠና ተደግፎ ተልዕኮውን መፈጸም ሲችል ነው ብለዋል።

የብሔራዊ ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ በቀጣይም ብቁ የሰው ኃይል ግንባታን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

የተመራቂዎች የትምህርት ውጤታማነት የሚለካው ወደ ፊት በሥራ ስምሪት ላይ በሚፈጥሩት ልዩነት ጭምር ነው ብለዋል።

የመረጃና ደኅንነት ሰራተኛ ሁልጊዜም በፈተና ውስጥ የሚያልፍ መሆኑን በመገንዘብ ለከፍተኛ ፈተና ራስን ማዘጋጀትና ያገኙትን እውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት ለሀገር አቅምና ደኅንነት መጠቀም እንዳለባቸው ገልጸዋል።


 

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው፤ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም ብቻ ሳይሆን በመረጃና ደኅንነት የሥነ-ልቦና ብቃት የበላይ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።

በዚህም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅና ብሔራዊ ደህንነትን ለማስከበር የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ጥልቅ ሪፎርም ማካሄዱን ገልፀዋል።

ሪፎርሙ በአሰራር፣ በአደረጃጀት፣ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂና በትብብርና አጋርነት ላይ ያተኮረ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ከየትኛውም ስጋት ለመጠበቅ መረጃን መሰብሰብና መተንተን የሚችል ብቁ የመረጃና ደህንነት የሰው ኃይል ግንባታ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ብሔራዊ ደህንነት ዩኒቨርሲቲ በሀገርና በህዝብ ላይ የሚቃጣ የስነልቦና ጥቃትን መመከት የሚችሉ በርካታ የመረጃ መኮንኖችና አመራሮችን በማፍራት ላይ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የዛሬ ተመራቂዎችም አሁናዊና የመጪ ጊዜ ስጋቶችን በመተንተን ሀገርና ህዝብን ከየትኛውም ስጋት የመጠበቅና ስትራቴጂካዊ የእውቀት የበላይነትን ለመያዝ መትጋት አለባቸው ነው ያሉት።

ብሔራዊ ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ከ40 በላይ ዓመታት በመረጃና ደህንነት ብቁ የሰው ኃይል የማፍራት ተልዕኮውን በመወጣት የአቅም ግንባታ ማዕከልነት ሚናውን እየተወጣ ይገኛል።

ዩኒቨርሲቲው በ2025 ዓ.ም በመረጃና ደኅንነት እንዲሁም በሥነ-ልቦና ጦርነት ትምህርትና ሥልጠና በአፍሪካ ቀዳሚ የልህቀት ማዕከል የመሆን ራዕይን ይዟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም