ቀጥታ፡

የኮደርስ ሥልጠና ወጣቱ ትውልድ በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ መሳተፍ የሚያስችለውን የዲጂታል ክህሎት እንዲኖረው የሚያስችል ነው  

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 23/2017(ኢዜአ)፡- የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ሥልጠናው ወጣቱ ትውልድ በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ መሳተፍ የሚያስችለውን ክህሎት እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ። 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ኮደርስ ሥልጠናን ላጠናቀቁ የተቋሙ ሠራተኞችና አመራሮች  እውቅና ሰጥቷል። 

እውቅና የተሰጣቸው ሠራተኞች ከአንድ እስከ ሦስት ባሉ የሥልጠና መርኃ ግብሮች ሥልጠናቸውን ወስደው ያጠናቀቁ መሆናቸውም ተጠቁሟል። 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ፤ በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ ለዲጂታል ክህሎት ግንባታ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል። 

ከዚህ አንጻር፤ የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ኮደርስ ሥልጠና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። 

ያም ብቻ ሳይሆን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግቦች እንዲሳካም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ገልጸዋል።

በመሆኑም ሰራተኞች አቅማቸውን በዚሁ መልክ ማሳደጋቸው በተቋማቸው የሚከናወኑ ሥራዎችን በብቃት ለመፈጸም እንደሚረዳቸውም አብራርተዋል።  

የሁሉም መሥሪያ ቤት ሰራተኞች የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን ተሞክሮ በመውሰድ ሥልጠናውን መከታተል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።


 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ (ዶ/ር) በበኩላቸው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽኑን እውን ለማድረግ ለሰው ኃይል ግንባታ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሁሉም አካል ርብርብ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።


 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በሁሉም ዘርፎች የሀገርን ዕድገት ለማረጋገጥ የዲጂታል ስትራቴጂ ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።

እውቅና የተሰጣቸው የተቋሙ ሰራተኞች እንዳሉትም ከሥልጠናው ሥራቸውን ማሳለጥ የሚያስችላቸውን እውቀት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

የኮድርስ ሥልጠና ሁሉንም የሚያሳትፍ በመሆኑም ማንኛውም ሰው የዚህ ሥልጠና ተሳታፊ በመሆን ያለውን እውቅትና ክህሎት ማሳደግ እንዳለበት ጠቁመዋል።

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር 132 ሰራተኞች የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ሥልጠና መከታተላቸው ተጠቁሟል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ይፋ የተደረገው የ''አምስት ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ’’ መርሃ ግብር በኢትዮጵያና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግሥታት የተጀመረ የዲጂታል ሥራ ክህሎትን የማሳደጊያ የትብብር ፕሮጀክት ነው።

ፕሮጀክቱ "ትውልድ ይማር፣ ትውልድ ይሰልጥን፣ ከዓለም ጋር ይፎካከር" በሚል እሳቤ ወጣቶች የቴክኖሎጂ እውቀታቸውን በማዳበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ብቁ ለማድረግ እየተተገበረ ይገኛል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ በሚገኘው በዚህ የኮደርስ ሥልጠና መርኃ ግብር እስካሁን ከ260 ሺህ በላይ ሰዎች ሥልጠናውን መውሰዳቸው ተገልጿል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም