ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክርና የተወካዮች መረጣ  ነገ እንደሚጀመር አስታወቀ

ቦንጋ ፤ ጥቅምት 23/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክርና የተወካዮች መረጣ መድረክ ነገ እንደሚጀመር አስታወቀ።

ከነገ ጀምሮ  እስከ ጥምት 30/2017ዓ.ም  በቦንጋ ከተማ በሚካሄደው በዚህ መድረክ ከ2 ሺህ 200 በላይ  ተሳታፊዎች እንደሚገኙ ተጠቁሟል።  

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች  ሙሉጌታ አጎ እና  ዘገየ አስፋው በቦንጋ ከተማ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው እንደተመለከተው፤  ኮሚሽኑ ቀደም ሲል በተለያዩ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራውን በተሳካ ሁኔታ ሲያከናወን ቆይቷል።

በሲዳማ፣ በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በሐረሪ፣ በአፋር፣ በሶማሌ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና በደበብ ኢትዮጵያ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች  ሂደቱ በተሳካ ሁኔታ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

ይህንኑ ወሳኝ ተግባር በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል  ከጥቅምት 24 2017 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

ለሂደቱ ስኬታማነት ኮሚሽኑ በቂ ቅድመ ዝግጅቶችን ማድረጉን ገልጸው፤  የመሰብሰቢያና የቡድን ውይይት ማካሄጃ ስፍራዎችን የማድረግ፣ የትራንስፖርትና ሌሎችም መሰናዶዎች መጠናቀቃቸውን አስረድተዋል።

በመድረኩም በክልሉ ከሚገኙ 57 ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች የተለዩ ከ2 ሺህ 200 በላይ ሰዎች የሕብረተሰብ ክፍል ተወካዮች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።

በተጨማሪም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመንግስት አካላት፣  የተለያዩ ተቋማትና ማህበራት ተወካዮች እንዲሁም ምሁራንና ተፅእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተሳታፊ እንደሚሆኑ አስታውቀዋል።

ተሳታፊዎች ተመካክረው አጀንዳዎቻቸውን በመለየትና በማጠናቀር ለኮሚሽኑ የሚያስረክቡ ሲሆን፤  ክልሉን በመወከል በአገራዊ ምክክር የሚሳተፉ  ተወካዮችን   እንደሚመርጡም በመግለጫው ተመልክቷል።

በክልሉ ከነገ ጀምሮ ለተከታታይ 7 ቀናት የሚደረገውን የምክክርና የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ስኬት ሁሉም  በንቃት እንድትሳተፍ፤ የክልሉ ሕዝብና ባለድርሻ አካላት ለሂደቱ ስኬት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ኮሚሽኑ መልዕክት አስተላልፏል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም