የጎንደር ከተማ የኮሪደር ልማትና የአፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግሥት የዕድሳት ሥራዎች የከተማዋን ገናና ታሪክ የሚመጥኑ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 23/2017(ኢዜአ)፡- በጎንደር ከተማ የሚካሄዱ የኮሪደር ልማትና የአፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግሥት የዕድሳት ሥራዎች የከተማዋን ገናና ታሪክ የሚመጥኑ መሆናቸውን የቱሪዝም ሚኒስትር ሠላማዊት ካሳ ገለጹ።

ሚኒስትሯ በጎንደር ከተማ የአቅመ ደካማ የቤት ዕድሳት የበጎ ፈቃድ ሥራን በማስጀመር በከተማዋ እየተገነቡ የሚገኙ የኮሪደር ልማትና የአፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግሥት የዕድሳት ሥራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

በዚሁ ጊዜ የቱሪዝም ሚኒስትር ሠላማዊት ካሳ፤ ጎንደር ታሪክና ባህል ጠገብ ውብ የመስህብ መዳረሻ ከተማ መሆኗን ተናግረዋል።

የአፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግሥት ዕድሳትና የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶችም የታሪክ አሻራዎችን የሚያስቀጥሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በጎንደር ከተማ የኮሪደር ልማትና የአፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግሥት የዕድሳት ሥራዎች የከተማዋን ገናና ታሪክ የሚመጥኑ ናቸው ብለዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ፤ የኢትዮጵያን ቅርሶች በመንከባከብ፣ በመጠገንና በመጠቀም ቱሪዝም ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ሚናውን እንዲወጣ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በዚህም ለቱሪዝም ዘርፉ አቅም የሚሆኑ የተሰናሰሉ የሆቴልና ሪዞርት፣ የመንገድ፣ የቴሌኮሙኒኬሽንና መሰል የመሰረተ ልማት ግንባታ መሰራታቸውንና በመሰራት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያውያንን ታሪካዊ፣ ባህላዊና ኃይማኖታዊ እሴቶች የመጠበቅ፣ የመንከባከብና የመጠቀም ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው፤ የከተማዋ የኮሪደር ልማትና የአፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግሥት የዕድሳት ሥራዎች አዲስ የሥራ ባህልን የፈነጠቁ ወሳኝ ፕሮጀክቶች ናቸው ብለዋል።


 

የከተማዋ ማኅበረሰብ በኮሪደር ልማት ሥራዎች ላይ በራሱ ተነሳሽነት የሚያደርገው ከፍተኛ ትብብር ፕሮጀክቶቹ በተሻለ የግንባታ ሂደት እንዲፋጠኑ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የከተማዋ የኮሪደር ልማትና የአፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግሥት የዕድሳት ሥራዎች የቱሪስት መስህብ መዳረሻ የሆነችውን ታሪካዊት ከተማ ውብ ገጽታ የሚያላብስ መሆኑን ተናግረዋል።

ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ልምድና ተምክሮ በመውሰድ በአሁኑ ወቅትም 14 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ሁለተኛ ምዕራፍ የከተማ ጎሪደር ልማት ለማከናወን የመንገድ ዳር ኮንቴይነርና አጥር በማንሳት ወደ ተግባር መገባቱን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም