የገጠር ኮሪደር አብነቱ የነዳዊት መንደር - ኢዜአ አማርኛ
የገጠር ኮሪደር አብነቱ የነዳዊት መንደር

የገጠር ኮሪደር አብነቱ የነዳዊት መንደር
ሀመልማላዊ ገጽታ የተላበሰ ውብ ቀዬ ነው፤ በጉራጌ ሰማይ ስር ከወልቂጤ ከተማ በስተምሥራቅ በአበሽጌ ወረዳ ጣጢሳ ቀበሌ ውስጥ ይገኛል።
መንደሩ ሰውና ተፈጥሮ የተዋደዱበት፣ አይነተ ብዙ አትክልትና ፍራፍሬ የተትረፈረፈበት፣ ሌማቱ የሞላበት፣ ሁሉ በእጅ ሁሉ በደጅ የሆነበት ስፍራ ነው።
በዚህ መንደር ምዕናባዊ መሻቱን በትጋት በተግባር ያረጋገጠ ለበርካቶች አብነት የሆነ ወጣት ይገኛል - ወጣት ዳዊት አሰፋ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ያስጀመሩትን የገጠር ኮሪደር ልማት በተግባር ለመኖር ቀድሞ የተነሳ ወጣት ነው።
የገጠር ኮሪደር የአርሶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ በመለወጥ ውብና ጤናማ የገጠር ከባቢ በመፍጠር የተሟላ ብልጽግና ማረጋገጥን ያለመ ነው።
የሁለት ልጆች አባት የሆነው ዳዊት ከተፈጥሮና ግብርና ጋር የተዋደደ ወጣት ሲሆን ለኑሮ የተመቸ ቀዬ ለመፍጠር አብዝቶ ይተጋል።
በዚህም ከነዳዊት መንደር እሸት አይታጣም፤ ወተትና እንቁላል ብርቅ አይደለም፤ ጓሮውም፣ ሌማቱም ሙሉ ነው። ከፍጆታ የዘለለ የገቢ ምንጭ ነው።
መንደሩ ለኑሮ የተመቸ፣ ቀልብን የሚስብ፣ ነፍስ በሀሴት የምትታከምበት፣ መንፈስ የሚታደስበት፣ ጽዱና የውብ ኑባሬ አብነት ነው።
ቀድሞውኑ በራሱ ጥረት ብዙ ርቀት የተጓዘው ዳዊት፤ በመንግስት በኩል ተነድፈው ወደ ትግበራ የገቡትን የሌማት ትርፋት እና በምግብ ራስን የመቻል ንቅናቄ በመተግበር የቀደመው የለም።
የ“30፣ 40፣ 30” የተሰኘው የክልሉ መንግስት የቤተሰብ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ንቅናቄ የተገበረበት መንገድ ለዚህ ማሳያ ነው።
አንድ አርሶ ወይም አርብቶ አደር በመጀመሪያ ዓመት 30፣ በሁለተኛው ዓመት 40 እና በሶስተኛ ዓመት 30 የፍራፍሬ ችግኞችን በመትከል ተጠቃሚ በሚሆንበት በዚህ መርሃ ግብር ዳዊት ከዕቅድ በላይ ማሳካት ችሏል።
ከዳዊት ጓሮ ከቡና እስከ ዘይቱና፣ ከብርቲካን እስከ አቮካዶ፣ ከሙዝ እስከ እንሰት፣ … ሌሎችም አትክልትና ፍራፍሬ አይነቶች አይታጡም።
ጠንካራ ዕጆች መሻቱን በግቢው በቀዬው እውን እንዲያደርግ ስላስቻሉት ከጨውና ዘይት በስቀተር ከገበያ የሚሸምተው አስቤዛ የለም።
ጓሮውን ለምግብነት በሚውሉ ዕጽዋት በመሸፈን የራስን ሀመልማላዊ ቀዬ አልምቶ የሚኖረው ዳዊት፤ “በአረንጓዴያማ መንደሬ ስኖር ነፍሴ አብዝታ ትደሰታለች” ይላል።
ጓሮውን በዕጽዋት ውብና ማራኪ ከማድረግ ባለፈ የገጠር አኗኗርን በማዘመን፣ ጤናማና ጽዱ ቀዬን ዕውን አድርጓል።
የሀገር በቀል ዕውቀት ማሳያ የሆኑ የቤተሰቦቹን ነባር ውብ የጉራጌ ጎጆ ቤቶች ከዘመኑ ጋር በማዋደድና የዘመኑን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ይታወቃል።
የነዳዊት መንደር የከተሜነት ኑባሬ በገጠር ውስጥ የተገለጠበት የኑሮ ዘይቤን ይከተላል።
መንግስት የገጠር ኮሪደር ልማትን በመጀመሩ በእጅጉ የተደሰተው ዳዊት የገጠር ኮሪደር ትሩፋት ብዙ መሆኑን ቀድሞ ተረድቷል።
የነዳዊት መንደር ከትርፍ አትክልትና ፍራፍሬ አልፎ የተንጣለለ የማኛ ጤፍ እና በቆሎ ማሳ ታጅቧል።
ከአራት ዓመታት በፊት በአንድ ሄክታር መሬት ላይ የጀመረው የመኸር እርሻ ዛሬ ወደ 20 ሄክታር ሰፍቷል።
ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር በመነጋገር በኩታገጠም እርሻ ቦቆሎ በስፋት ያለማል፤ ለክልሉ ምርጥ ዘር ድርጅት የጤፍ ምርጥ ዘር ያባዛል።
"ከልጅነቴ እርሻ እወዳለሁ" የሚለው ዳዊት፤ ግብርናን እሴት ጨምሮ በማዘመን ስኬታማ አርሶ አደር ሆኗል።
በተለይም ከቀለበሌ እስከ ወረዳ ባለው የመንግስት መዋቅር የተደረገለት ድጋፍና ክትትል ለዳዊት ስኬታማነት ቁልፍ አስተዋፅኦ አበርክቷል።
ዳዊት የግብርና ስራውን ከማስፋት ባለፈ ገና ያልተገበራቸው ሌሎች አዳዲስ ውጥኖችም አሉት።
በተለይም የውሃና የመሬት አቅርቦት ጽኑ ፍላጎቱ በመንግስት ቢሟላለት ከራሱ ባሻገር ለአካባቢው ወጣቶችና አርሶ አደሮች ኑሮና ሕይወት የመለወጥ ርዕይ ሰንቋል።
በዚህ ዘመን በትጋት ከተሰራ መለወጥ ይቻላል፤ ወጣቱ መዘናጋት የለበትም የሚል ብርቱ ጥሪ አቅርቧል።
ዳዊት አሰፋ ራስን ከመቻል ባሻገር ለሌሎች የቀዬው ወጣቶች አርዓያ ሆኗል።
ዳዊትን ለመሆን፣ የዳዊትን አሻራ ለማስፋት የሚሹ የቀየው ወጣቶች ብዙ ናቸው።
የዳዊት አርዓያነት ከሀሳብ ባለፈ ወጣቶችን በተጨባጭ እየደገፈ እና እያቀፈ የራሳቸው ጥሪት እንዲያፈሩ፣ እርሱን እንዲከተሉ እያደረጋቸው ነው።
ለዚህም ከዳዊት ተጠግተው የራሳቸውን ስኬታማ ጉዞ የጀመሩት አብዱልሻክ ረሻድ እና ጴጥሮስ ጸጋዬ ምስክሮች ናቸው።