ምክክሩ ለአሁናዊና ሲንከባለሉ ለመጡ ችግሮች መፍትሄን ያመላክታል- አስተያየት ሰጪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ምክክሩ ለአሁናዊና ሲንከባለሉ ለመጡ ችግሮች መፍትሄን ያመላክታል- አስተያየት ሰጪዎች
ቦንጋ ፤ጥቅምት 23/20217 (ኢዜአ):- ምክክሩ ለአሁናዊና ሲንከባለሉ ለመጡ ችግሮች መፍትሄን ያመላክታል የሚል እምነት እንዳላቸው አስተያየታቸውን የሰጡ የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
የምክክር ኮሚሽኑ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክን ጥቅምት 24/2017 ዓ.ም ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ማጠናቀቁን መግለፁ ይታወሳል።
ጉዳዩን አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች ምክክሩ አሁናዊና ከዚህ ቀደም ሲንከባለሉ ለመጡ ችግሮች መፍትሄን ያመላክታል የሚል እምነት እንዳለቸው ገልፀዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የኢንጂነሪንግ ትምህርት መምህር አዛርያስ አየለ ምክክሩ ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማት መጠናከር ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል።
በምክክርና በንግግር የማይፈታ ችግር የለም የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸው በመሆኑም ሁላችንም ያለንን ቅሬታ ወደ ውይይት በማምጣት የምንፈልገውን ሰላም ለማምጣት መትጋት ይጠበቅብናል ብለዋል።
የምክክር ሂደቱ አሳታፊና አካታች ሆኖ እንዲፈጸም የሁሉም ቀና ትብብር እንደሚያስፈልግ ገልፀው ሀገርን በሚያሻግሩና አንድ በሚያደርጉ ትርክቶች ላይ በማተኮር መመካከር እንደሚገባም ገልጸዋል።
የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ጋዜጠኛ ዮሐንስ ክፍሌ በበኩሉ፣ አለመግባባቶችንና የሀሳብ ልዩነቶችን በንግግርና በውይይት መፍታት አለመቻል የበርካታ ችግሮች መንስኤ መሆኑን ገልጿል።
ያለንን የመነጋገርና የውይይት እሴቶች በማዳበር ልዩነቶቻችንን በምክክር በማጥበብ መግባባት ላይ መድረስ ወቅቱ የሚጠይቀው የሰለጠነ አካሄድ ነው ብሏል።
ስለሆነም እንደሃገር የተቋቋመው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አካታችና አሳታፊ በመሆኑ ያሉ ችግሮችን በምክክር በመፍታት መፍትሄን ያመጣል ብሎ እንደሚያምንም ገልጿል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ በበኩላቸው ዘላቂ ሰላምን ማስፈን ሀገራዊ ምክክሩ እንዲያሳካ ከሚጠበቅበት አይነተኛ አላማዎች መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።
ምክክሩ ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን ከመፍታት ባሻገር በቀጣይም ሊያጋጥሙ የሚችሉ አለመግባባቶችንና የሀሳብ ልዩነቶችን በመነጋገር የመፍታት ባህልን ማዳበር የሚያስችል መሰረትን የሚጥል ነው ብለዋል።
ኮሚሽኑ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከጥቅምት 24 ጀምሮ ለ7 ቀናት የሚቆይ የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ ማካሄድ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ የምክክር ሂደቱ አሳታፊና አካታች እንዲሆን የተለያዩ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸው በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉ ወገኖችን ጭምር ወደ ምክክሩ ለማምጣት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በክልሉ በሚደረገው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ በንቃት በመሳተፍ የህብረተሰቡንና የሀገሪቱን ችግሮች በጥልቀት ለመዳሰስ ፋይዳ ያላቸው አጀንዳዎችን ማቅረብ እንደሚገባም አሳስበዋል።