ዛሬ በአዲስ አበባ የተመረቁት የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ማምረቻ ማዕከልና ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶች

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዛሬ በአዲስ አበባ ያስመረቃቸው የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ማምረቻ ማዕከልና ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶች እውነታ

የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ማምረቻ ማዕከል፤-

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ ያስገነባውን የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ማምረቻ ማዕከል በራስ አቅም በ1 ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባ ነው።

አንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአማካሪነት እና ቢኤም ቴክኖሎጂ በተቋራጭነት ተሳትፈዋል፤ የኮንክሪት ውህድ እና የብሎኬት ፋብሪካን በውስጡ ይዟል።

የኮንክሪት ውህድ ፋብሪካው አርማታ በቀን 24 ሰዓት የመስራት አቅም ያለው ሲሆን ለ 8 ሰዓት ብቻ ቢሰራ በአመት 202 ሺህ 752 ሜትር ኪዩብ የማምረት አቅም እንዳለው ተመላክቷል።

ፋብሪካው ባለ 20 ሴ.ሜ ብሎኬት በ8 ሰአት 25 ሺህ የማምረት አቅም ያለው ሲሆን ባለ 10 እስከ 50 ሺህ እንዲሁም ባለ 15 እስከ 37 ሺህ ብሎኬት ማምረት እንደሚችልም ተገልጿል።

የብሎኬት ምርቶቹ ከፍተኛ የጥራት መለኪያ መስፈርትን ያሟሉና ለመንገድ ንጣፍ የሚሆኑ ታይልሶች በብዛት እና በጥራት የማምረት ተጨማሪ አቅም ያለው ነው።


 

ፋብሪካው በዓመት 4 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ የማስገኘት አቅም ያላው እንደሆነም ታውቋል።

የኮከበ ጽባህ ሳይት ዘመናዊ መኖርያ ቤትና የንግድ ማዕከል

በኮከበ ጽባህ ህንጻ፤ ከንግድ ቤት በተጨማሪ ከባለ 2 እስከ ባለ 4 መኝታ ክፍል ያላቸው ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶችን ያካተተ ነው።

ከቀበና ተፋሰስ የልማት ስራ ጋር በተያያዘ ማራኪ ገጽታ የተላበሰ አካባቢ ላይ ይገኛል፤ ራሱን የቻለ ግቢ ውብና አረንጓዴ ስፍራ ያለው ባለ ሁለት ብሎክ ነው።

ዘመናዊ ቤቶቹ ከንግድ ቤት በተጨማሪ ከባለ ሁለት እስከ ባለ አራት መኝታ ክፍል ያላቸው ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶችን ያካተተ ነው።

ግንባታው ሜስኮን የኮንስትራክሽን ድርጅት ሲያከናውን የግንባታ አማካሪ ድርጅቱ ደግሞ አኪዩት ኢንጅነሪንግ ነው፤ ሳይቱ 1 ሺህ 263 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን እስከ 148 ካሬ ድረስ ስፋት ያላቸውን ዘመናዊ ቤቶች የያዘ ነው።

የምስራቅ አጠቃላይ ሳይት ዘመናዊ መኖርያ ቤትና የንግድ ማዕከል

ምስራቅ አጠቃላይ ትምህርት ቤት አካካቢ የሚገኘው ምስራቅ አጠቃላይ ሳይትም ከንግድ ቤት በተጨማሪ ስፋታቸው እስከ 218 ካሬ ሜትር የሚሆኑ ከባለ 1 እስከ ባለ 4 መኝታ ክፍል ያላቸው ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች መያዛቸው ተገልጿል።

ሳይቱ ለኑሮ ምቹና ነፋሻማ በሆነው አካባቢ የምስራቅ አጠቃላይ ትምህርት ቤት አካባቢ የሚገኝ ሳይት ነው።

ህንጻው ባለ 13 ወለል ሲሆን ከንግድ ቤት በተጨማሪ ስፋታቸውን እስከ 145 ካሬ የሚሆኑ ከባለ 1 እስከ ባለ 4 መኝታ ክፍል ያላቸው ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች ያካተተ ሲሆን፤ ህንጻው 1 ሺህ 541 ካሬ ላይ ያረፈ ነው።

በምረቃ መርሀ ግብሩ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር እንዲሁም የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ ዓለምጸሀይ ጳውሎስን ጨምሮ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር)፣ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ፋብሪካውንና ዘመናዊ ቤቶቹን ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች መርቀው ስራ አስጀምረውታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም