በጎንደር ከተማ ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ወደ ትግበራ መግባቱ ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር ከተማ ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ወደ ትግበራ መግባቱ ተገለፀ
ጎንደር፤ ጥቅምት 23/2017(ኢዜአ)፡- በጎንደር ከተማ ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት የቅድመ ዝግጅት ስራ ተጠናቆ ወደ ትግበራ መሸጋገሩን የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አስታወቁ።
የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የኮሪደር ልማት የከተማዋን ጥንታዊነት በጠበቀ አግባብ እየተከናወነ ይገኛል።
በዚህም በመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት የተገኘውን ተሞክሮ በማስፋት የሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት መከናወን መጀመሩን ገልፀዋል።
ሁለተኛው ምዕራፍ 12 ኪሎ ሜትር የመንገድ ክፍል የሚለማ ሲሆን ከፒያሳ እስከ አየር ማረፊያ ያለውን የሚሸፍን መሆኑንና የዲዛይን ስራው ተጠናቆ ወደ ትግበራ መገባቱን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም የመንገድ ዳር ኮንቴይነሮችንና ህገወጥ አጥሮችን የማንሳት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ተነሺዎችንም በሶስት ክላስተሮች በተደራጁ ቦታዎች ዳግም ስራ እንዲጀምሩ ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱ ህንጻዎችን የማስዋብ፣ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶችን የመገንባት እንዲሁም የመንገድ ዳር መብራቶችን የመትከልና የአስፓልት ማንጠፍ ስራዎችን ያካተተ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
እንዲሁም የአረንጓዴ ስፍራዎችና የመዝናኛ ፓርኮች ግንባታን ጨምሮ የመብራት፣ የውሃ፣ የስልክና የኢንተርኔት መስመሮችም አንድ ወጥ በሆነ መንገድ እንደሚዘረጉ ገልጸዋል፡፡
ፒያሳንና የአጼ ፋሲል ቤተ መንግስት ዙሪያን ያካተተውና አንድ ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት በጥሩ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱ አዲስ የስራ ባህልን ከመፍጠሩ በላይ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ የልማት መነሳሳትን መፍጠሩን ጠቁመው፤ ለበርካታ ወገኖችም የስራ እድል ለመፍጠር ያስቻለ ፕሮጀክት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ህዝቡ የኮሪደር ልማቱን በሙሉ ልብ በመደገፍ በባለቤትነት ስሜት እየተሳተፈ ነው ያሉት አቶ ቻላቸው ፕሮጀክቱን በፍጥነት ለማጠናቀቅም ምሽት ጭምር በፈረቃ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱ በጥር ወር በታላቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ስርዓት የሚከበረውን የጥምቀት በዓል በልዩ ድባብ ለማክበር ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ለከተማው የቱሪስት ፍሰት ማደግም አዎንታዊ ሚናው ከፍ ያለ እንደሆነ አብራርተዋል።
በከተማው የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ሲሆን ህዝቡ የሰላሙና የልማቱ ባለቤት በመሆን የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል፡፡