ኮርፖሬሽኑን ወደ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ለሚያደርገው ሽግግር ስራዎችን ፍጥነትና ጥራት በታከለበት ሁኔታ ማከናወን ይገባል - ፍሰሃ ይታገሱ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 23/2017(ኢዜአ)፡- የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ወደ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ለሚያደርገው ሽግግር ስራዎችን በፍጥነት እና በተሻለ ጥራት ማከናወን እንደሚገባ የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ(ዶ/ር) ገለጹ።

ኮርፖሬሽኑ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ግምገማውን በቢሾፍቱ ከተማ አካሂዷል።

ኮርፖሬሽኑን ወደ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ለማሸጋገርና ትርፋማነቱን ለማሳደግ አዳዲስ የስራ ዘርፎች እንደሚጀምር ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።

የተቋማዊ ሪፎርም ግንባታ ስራውን ማፋጠን፣ ተቋሙን የሚመጥን አመራርና ሰራተኛ ማፍራት፣ አዳዲስ ዘርፎችን መለየት እና መጨመር እንዲሁም ስራን በላቀ ጥራት መፈጸም ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸውንም አመልክተዋል።

ተቋሙ በተያዘው በጀት ዓመት የማስፋፊያ ስራዎችን በፓርክ ደረጃ ለመጀመር እቅድ መያዙን ጠቁመዋል።

ኮርፖሬሽኑ በሆቴል፣ በማማከር እና በስልጠና፣ በኮንስትራክሽን፣ በሎጀስቲክስ እና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ራሳቸውን የቻሉ ተቋማትን ለመመስረት ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን አመልክተዋል።

ወደ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ የሚደረገውን ጉዞ ሁሉም አመራር በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እና በተቀናጀ አግባብ መምራት እንዳለበትም አሳስበዋል።

ኮርፖሬሽኑ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሶስት ወራት 300 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ አዳዲስ ኢንቨስትመንት መሳቡ በግምገማው ወቅት ተነስቷል።

ኮርፖሬሽኑ በስሩ የሚያስተዳድራቸው ፓርኮች ውስጥ ያሉ ባለሀብቶች ከ26 ሚሊየን ዶላር በላይ የሚገመት ምርት ለውጪ ገበያ ማቅረባቸው ተጠቁሟል።

በተጨማሪም ተቋሙ በሩብ ዓመቱ 864 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱንም አስታውቋል።

ዋና ስራ አስፈጻሚው በተቋሙ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸም ግምግማ ላይ የቀጣይ 3 ወራት የስራ አቅጣጫና መመሪያ መስጠታቸውን ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም