ለህብረተሰቡ ተገቢ አገልግሎት በመስጠት የአካባቢያቸውን ልማት ለማፋጠን በትኩረት እንደሚሰሩ ሰልጣኝ አመራሮች ገለጹ

ዲላ/ሚዛን አማን፤ ጥቅምት 22/2017(ኢዜአ) ፦ ለህብረተሰቡ ተገቢና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የአካባቢያቸውን ልማት ለማፋጠን በትኩረት እንደሚሰሩ  በዲላና ሚዛን አማን ከተሞች ስልጠና የወሰዱ አመራሮች ገለጹ።

በጌዴኦ ዞን ዲላ ማዕከልና በሚዛን አማን ከተማ "የህልም ጉልበት ለእመርታዊ ለውጥ" በሚል መሪ ሀሳብ ሲሰጥ የቆየው ሦስተኛ ዙር የመንግሥት አመራር የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጠናቋል።

በዲላ ማዕከል ስልጠናውን ከወሰዱ አመራሮች መካከል ወይዘሮ ዝናሽ በቀለ እንዳሉት፣ ስልጠናው ለተሻለ ልማትና እድገት እንዲሰሩ የአመራር አቅማቸውን አሳድጎላቸዋል።

በአካባቢያዊና ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ ግንዛቤያቸውን ከማሳደግ ባለፈ ለህብረተሰቡ አንገብጋቢ የልማት ችግሮች ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም እንዳገኙም ተናግረዋል።

ስልጠናው ንድፈሀሳብን ከመስክ ምልከታ ጋር ማስተሳሰሩን ገልጸው፣ በቀጣይ ውጤታማ የልማት ሥራዎችን በማከናወን የአካባቢያቸውን ልማት ለማፋጠን መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።   

ስልጠናው በሀገራዊ ለውጡ የመጡ ውጤቶችን ለማስቀጠል አዲስ አስተሳሰብና አዲስ አቅም የፈጠርንበት ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛው ሰልጣኝ አቶ አለማየሁ ጅግሶ ናቸው።

አመራርነት የህዝብ አገልጋይነት በመሆኑ የህብረተሰቡን ችግር አድምጦ ፈጥኖ ለመፍታትና በልማት ተጠቃሚ ለመሆን በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።

ከጌዴኦ ዞን አስተዳደር አመራሮች መካከል አቶ አበባየሁ ኢሳያስ በበኩላቸው በማዕከሉ 687 የመንግሥት ሥራ ሃላፊዎች በንድፈ ሃሳብና በተግባር የታገዘ ስልጠና መውሰዳቸውን ነው የገለጹት።

ስልጠናው የአመራሩን አቅም ከመገንባት ባለፈ በቀጣይ ለተሻለ ልማትና እድገት እንዲሠራ ዕድል የፈጠረ ነው ብለዋል።

በተመሳሳይ ዜና በቤንች ሸኮ ዞን ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ፀጋ በማልማት የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰሩ የዞኑ አመራር አካላት ገልጸዋል።

አስተያየታቸውን ከሰጡ የቤንች ሸኮ ዞን አስተዳደር አመራሮች መካከል አቶ ደግፌ ኩድን በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ እንዳሉት፣ በየደረጃው አመራሩ የአስተሳሰብ ለውጥ አምጥቶ ሕዝብን እንዲያገለግል እየተሠራ ነው።

በስልጠናው  አብሮነት ላይ የተመሠረተ ለውጥ ለማስመዘገብ የሚችል የአመራር አቅም እየተፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተለይ የዞኑን እምቅ የተፈጥሮ ፀጋ በማልማትና እሴት በመጨመር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በስልጠናው መግባባት ላይ እንደተደረሰና ለዚህም እንደሚሰራ አመልክተዋል።

አመራሩ የመንግሥትን እጅ ሳይጠበቅ የአካባቢውን ሀብት ለልማት በማዋል ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚችል ግንዛቤ የተያዘበት መሆኑንም አስረድተዋል።

ከስልጠናው ተሳታፊ አመራሮች መካከል አቶ ስንታየሁ ጋይድ በሰጡት አስተያየት ስልጠናው ከአካባቢ አልፎ ሀገራዊ ነባራዊ እውነታን እንድንገነዘብ አስችሎናል ብለዋል።

እንደ አመራር የማዘዝና ሪፖርት የመቀበል ባህልን በመተው ባለን አቅም ራሳችን ሠርተን ማሠራት እንዳለብን ግንዛቤ ያገኘንበት ስልጠና ነው ሲሉም አክለዋል።

በቀጣይም ሕዝብን ያሳተፈና በመግባባት ላይ የተመሠረተ የልማት ሥራ ለማከናወን ቁርጠኛ መሆናቸውንም አቶ ስንታየሁ ተናግረዋል።

ስልጠናው በፈጠረላቸው አቅም ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት በመስጠት በልማት ሥራ አንድ እርምጃ ወደፊት ለመራመድ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ትዕግስት ለማ ናቸው።

በጌዴኦ ዞን ዲላ ማዕከልና በሚዛን አማን ከተማ በተሰጠው ስልጠና የተሳተፉ አመራሮች 410 ሺህ ብር በማሰባሰብ ለትምህርት ቤት ካደረጉት ድጋፍ ባለፈ ደም በመለገስና አቅመ ደካሞችን በመደገፍ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣታቸው ታውቋል። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም