ቀጥታ፡

የቱሪዝም ፓኬጅ በማዘጋጀት የኮንፍረንስ ቱሪዝምን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 22/2017(ኢዜአ)፦የቱሪዝም ፓኬጅ በማዘጋጀት የኮንፍረንስ ቱሪዝምን ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትናንትናው ዕለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ባለፉት ሦስት ወራት ከ20 የማያንሱ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶች መስተናገዳቸውን ገልፀዋል።

ለዚህም የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የለሙ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች በአገሪቱ የኮንፍረንስ ቱሪዝም እንዲያድግ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን የመጎብኘት ፍላጎት እያደገ እንዲመጣ ማስቻሉን አስረድተዋል።  

በቅርቡም ኢትዮጵያ የተለያዩ ኮንፍረንሶችን እንደምታስተናግድ በቱሪዝም ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ኮንቬንሽን ቢሮ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ጌትነት ይግዛው ለኢዜአ ገልፀዋል። 

አሁን ላይ የኮንፍረንስ ቱሪዝም እያደገ መምጣቱን ገልጸው፤ ለዚህም በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎች ልማት ሥራዎች ለኮንፍረንስ ቱሪዝም ምቹ ሁኔታን መፍጠራቸውን እንደ ዋና ምክንያት ገልፀዋል። 

ቱሪዝም ዘመናዊነትን ይጠይቃል ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፤ እነዚህ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች ጎብኚዎች በሚያደርጉት ቆይታ የለመዱትን ዓይነት ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ማግኘት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

የኮንፍረንስ ቱሪዝም መበራከት የአገሪቱን የቱሪዝም እንቅስቃሴ የሚያጎለብትና ከዘርፉ የሥራ ዕድልን ጨምሮ  ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ለማግኘት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያን የማስተዋወቅና የኮንፍረንስ ቱሪዝምን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ለዚህም በተለይም የቱሪዝም ፓኬጅ በማዘጋጀት በተለያዩ አካባቢዎች ጉብኝት በማድረግ ኢትዮጵያን ይበልጥ ለማወቅ የሚያስችል ተግባር እንደሚከናወን ጠቁመዋል። 

የኤልጌል ሆቴል ኦፕሬሽን ማናጀር አዲሱ ገብረማርያምና የሪሊያንስ አፍሪካ አስጎብኚና የጉዞ አገልግሎት ሥራ አስፈጻሚ ዑስማን መሀመድ፤ አዲስ የለሙ የቱሪስት መዳረሻዎች የቱሪስት ፍሰትን ለማሳደግ አስተዋፅዖ እያበረከቱ ነው ብለዋል።

እነዚህን የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች ይበልጥ በማስተዋወቅ የቱሪዝም ፍሰቱን ለመጨመርና የኮንፍረንስ ቱሪዝም ለማጠናከር እንደሚሰራ ተናግረዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም