ቀጥታ፡

በሚቀጥሉት አሥር ቀናት በደቡብ አንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የዝናብ መጠንና ሥርጭት ቀጣይነት ይኖረዋል 

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 22/2017(ኢዜአ)፦በሚቀጥሉት አሥር ቀናት በደቡብ ምዕራብ፣ ደቡብና ደቡብ ምስራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ የዝናብ መጠንና ሥርጭት ቀጣይነት እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ። 

ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ፤ የመጀመሪያዎቹ አሥር ቀናት በደቡብና በደቡብ ምሥራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ የዝናቡ መጠንና ሥርጭት ቀጣይነት ይኖረዋል ብሏል። 

በሌላ በኩል በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ላይ የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ እንደሚስተዋልም ገልጿል።  

በሚቀጥሉት ቀናት ዝናብ ሰጭ የአየር ሁኔታ ክስተቶች በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብና ደቡብ ምስራቅ እንዲሁም በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ አከባቢዎች ላይ የተሻለ ገጽታ እንደሚኖራቸውም ተመላክቷል።

በመሆኑም በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የቦረናና ጉጂ ዞኖች፤ የሲዳማ ክልል ዞኖች፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖችና የሶማሌ ክልል ደቡባዊ ዞኖች ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው ተጠቅሷል።

በተጨማሪም በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ ዝናቡ በተመሳሳይ ሁኔታ ቀጣይነት  እንደሚኖረም ተገልጿል።

እንዲሁም በፀኃይ ኃይል ታግዞ ከሚጠናከሩት የአየር ሁኔታ ክስተቶች ላይ በመነሳት በምዕራብና ቄለም ወለጋ፣ ኢሉባቦር፣ ቡኖ በደሌ፤ ከፋ ሸካ ቤንች ሸኮና ዳዉሮ፤ ማጅንግ ዞን፤ እና  በጥቂት ሥፍራዎች ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉም ተብሏል።

በቀጣይ አሥር ቀናት የሚኖረው እርጥበት ቀደም ብለው ለተዘሩና ፍሬ በማፍራት ላይ ለሚገኙ ሰብሎች፣ ዘግይተው ተዘርተው በተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሰብሎች፣ ለቋሚ ተክሎች አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።

በተጨማሪም ለአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት ከማሻሻል አንፃር የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተጠቁሟል።  

በተጓዳኝም፤ አብዛኛው ገናሌ ዳዋ፣ ዋቤ ሸበሌ፣ ኦሞ ጊቤ፣ ባሮ አኮቦ፣ ታችኛው አባይ፣ መካከለኛና ታችኛው ስምጥ ሸለቆ የተለያየ ደረጃ ያለው እርጥበት ያገኛሉ ተብሏል። 

በሌላ በኩል በተለይም ውኃ አጠር በሆኑ አካባቢዎች የሚገኘውን የዝናብ ውኃ ለመሰብሰብና ለማከማቸት መልካም አጋጣሚ ስለሚያገኙ ይህንኑ ለማከናወን የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል። 

የሚኖረዉ የእርጥበት ሁኔታ በተለይም በመጀመሪያዎቹ ቀናቶች ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ቀላል መጠን ያለዉ ዝናብ ከመኖሩ ጋር ተዳምሮ በመኸር ሰብል ስብሰባና ድኅረ ሰብል ሰብሰባ ተግባራት ላይ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል አርሶ አደሮችም ሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ልዩ ትኩረት በመስጠት የደረሱ ሰብሎችን በሚኖሩት ደረቅ ሰሞናት የመሰብሰብና በአግባቡ የመከመር ተግባራትን ለማከናወን አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል ብሏል ኢንስቲትዩቱ። 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም