ቀጥታ፡

ሰላም ለማፅናት እየተከናወነ ባለው እንቅስቃሴ የህብረተሰቡ ድጋፍ አበረታች ነው- ብርጋዴር ጀኔራል ኤርቃሉ ዱካቶ

መተማ ፤ ጥቅምት 22/2017 (ኢዜአ)፡-  ሰላምን ለማፅናት  እየተከናወነ ባለው የህግ ማስከበር እንቅስቃሴ የህብረተሰቡ ድጋፍ  አበረታች መሆኑን  የ504ኛ ኮር ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል ኤርቃሉ ዱካቶ  ገለጹ። 

''ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም'' በሚል መሪ ሃሳብ  ህዝባዊ የውይይት መድረክ በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሃ ከተማ ተካሄዷል።

በዚህ ወቅት ብርጋዴር ጄነራሉ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ መከላከያ ሰራዊት ሰላም አደፍራሽ የሆነውን ፅንፈኛ ቡድን ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ ህግ እንዲከበር እያደረገ ይገኛል።

"ከዚህ በፊት ፅንፈኛው በህዝቡ ላይ ያልተገባ ወሬ በማናፈስ ለማደናገር ሞክሮ ነበር" ያሉት አዛዡ አሁን ላይ አብዛኛው ማህበረሰብ የጽንፈኛውን ዓላማ በግልፅ መረዳት መቻሉን ተናግረዋል።

መንግስት ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በሚያደርገው የህግ ማስከበር ስራ ህብረተሰቡ ለፀጥታ አካሉ እየሰጠ ያለው ድጋፍ አበረታች  መሆኑን ገልጸዋል።

ህዝቡ ከሎጅስቲክ ድጋፍ ጀምሮ ከሰራዊቱ ጎን ሆኖ ፅንፈኛውን መዋጋቱን ጠቅሰው፤ በቀጣይም የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ በመቀጠል ዘላቂ ሰላምን ማፅናት እንዳለበት አሳስበዋል።


 

የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪ መልዓከሀይል ዘሚካኤል ሞገስ በሰጡት አስተያየት፤  መንግስት እየወሰደ ባለው የህግ ማስከበር እርምጃ   ሰላም መስፈኑን ተናግረዋል።

ሰላሙን በዘላቂነት ለማስጠበቅ ህዝቡ ከፀጥታ አካሉ ጎን ሆኖ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ የሚጠበቅ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ሌላኛው በመተማ ወረዳ የኮኪት ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሙሃመድ ጌታሁን በበኩላቸው፤ ቀበሌያቸው በፅንፈኛው ኃይል ተይዞ በነበረበት ወቅት ሀብትና ንብረታቸው  የወደመና የተዘረፈ መሆኑን አስታውሰዋል።

በጥሬ ብር 197 ሺህ ብር፣ 20 ኩንታል ጤፍና ሙሉ የሱቅ ሸቀጥ እንደተዘረፈባቸው ጠቅሰው፤ መንግስት እየወሰደ ባለው የህግ ማስክበር  ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።


 

ሌላኛው ተሳታፊ አቶ ሁሴን አህመድ፤  ወደ እርሻ ልማት ስራቸው ለመሄድና ለማልማት ፅንፈኛ ኃይሉ ተፅዕኖ ፈጥሮባቸው እንደቆየ አውስተዋል።

ችግርን በውይይት መፍታት እንጂ  በሀይል ለማድረግ መሞከር ተገቢነት እንደሌለው ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም